ቀጥታ፡

ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂን በጥሩ ሁኔታ ለመቀበል ዝግጁ ነን-የአዲስ አበባ ነዋሪዎች

አዲስ አበባ ሀምሌ 6/2010 የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ አዲስ አበባ ሲገቡ ጥሩ አቀባበል ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተናገሩ። ፕሬዝዳንቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባቀረቡላቸው ግብዣ መሰረት ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ከፍተኛ የልዑክ ቡድን ይዘው ነገ አዲስ አበባ እንደሚገቡ ይጠበቃል። በኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች መካከል ለሁለት አስርት ዓመታት ተፈጥሮ የነበረውን "ሞት አልባ ጦርነት" በመናድ ወንድማማችነታቸውን በአዲስ ታሪክ በማደስ ዘርፈ-ብዙ እንቅስቃሴዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። ኢዜአ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎችም የሁለቱን አገራት ወንድማማች ህዝቦች ሰላም በማስቀጠልና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙቱን ለማጠናከር፤ ብሎም ፍቅራቸውን ለማደስ የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፉ ገልጸዋል። በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኤርትራ የተደረገላቸውን ደማቅ አቀባበል በማድነቅ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ መልካም አቀባበል ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ነው የተናገሩት። የአዲስ አበባ ነዋሪ ወጣት አለማየው አሰፋ በሰጠው አስተያየት"ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ለመቀበል ከ20 ዓመት በኋላ ነው ፤እሳቸውን መመቀበል ማለት የኤርትራን ህዝብ በፍቅር መቀበል ማለት ነው፤ የኤርትራ ህዝብ ያሳየንን ፍቅር እኛም እዚ በመድገም ለማሳየት ዝግጅት ላይ ነን ያለነው˝ ብሏል፡፡ ወጣቱ  ነገን በጉጉት እየጠበቁ  መሆናቸውንና   ኢትዮጵያዊያን የሚታወቁበትን የእንግዳ መቀበል ባህል  በአለም  መድረክ የሚታይበት  በመሆነ  በጨዋነት ማሳየት አለብን ነው ያለው ፡፡ " የኢትዮጵያ ህዝብ በፍቅር እንደሚወጣና እንደሚቀበላቸው ምንም ጥርጥር የለውም፤ ይህ ህዝብ ደግሞ ይህንን ነገር ሲመኘው ሲፈልገው የነበረው ስለሆነ በጣም ደስ ብሎት ነው በፍቅር የምንቀበላቸው ይህ  የሚያሳየን ነገር የመነፋፈቅ ወንድማዊነትን ነው"  በማለት የጠቀሰው የከተማው ነዋሪ አቶ ሲሳይ ዲያ ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ኤርትራን በጎበኙበት ወቅት በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል በዲፕሎማሲ፣ በትራንስፖርት፣ በድንበር ጉዳዮች፣ በወደብ አጠቃቀም፣ በንግድ እንዲሁም በአፍሪካና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም