ቀጥታ፡

ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ ስኬታማነት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል- የኅብረቱ አመራሮች

አርባ ምንጭ ፣ ነሐሴ 29/2012(ኢዜአ) ለ2013 የትምህርት ዘመን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ ስኬታማነት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ኅብረት አመራሮች አሳሰቡ።

39ኛው የኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ኅብረት ጉባዔ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ተካሂዷል።

በዚህ ወቅት አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የኅብረቱ አመራሮች እንዳሉት ሰላማዊ የመማር ማስተማሩ ሥራ ካለ ተማሪዎች ተሳትፎ ሊሳካ አይችልም።

ከጉባዔው ተሳታፊዎች መካከል የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ኅብረት ፕሬዝዳንት ተማሪ ኢያሱ ጌቱ በሀገሪቱ በነበረው የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ልዩነቶች ሳቢያ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ አሉታዊ ጫና ሲያሳድር መቆየቱን አውስቷል።

በዚህም ምክንያት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በርካታ የሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳቶች እንደደረሱ ተናግሯል።

ማንም ብሔሩን መርጦ የተፈጠረ የለም ያለው ተማሪ ኢያሱ ሁሉም የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ከዚህ ዓይነቱ ኋላቀር አመለካከት በመውጣት ለቀጣዩ የትምህርት ዘመን ስኬታማነት የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስቧል።

ለዚህ እውን መሆን በተፈጥሮ የተሰጠንን ፀጋ አምነን በመቀበል በምንማርበት ዩኒቨርሲቲ እርስ በርስ በመከባበር፣ መቻቻል፣ ፍቅር ተሳስበንና ተግባብተን የመጣንበትን ዓላማ ለማሳካት መትጋት ይጠበቅብናል ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኅብረት ፕሬዝዳንት ተማሪ ኦሊ በዳኔ በበኩሉ ከመላ ሀገሪቱ ወደ ዩኒቨርስቲ የሚመጡ ተማሪዎች የተለያየ ባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክና ሃይማኖት ያላቸው እንደመሆኑ መጠን ልዩነታችንን እንደ መልካም ፀጋ ልንቀበል ይገባል ብሏል።

ብዝሃነታችን ውበት እንጂ ሥጋት ሊሆን አይገባም ያለው የኅብረቱ ፕሬዝዳንት ካሁን በፊት በዩኒቨርሲቲዎች ከደረሰው ጉዳት መማር ተገቢ እንደሆነም ጠቁሟል።

ለመጪው የትምህርት ዘመን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ ስኬታማነተ ተማሪዎች በኢትዮጵያዊ ጨዋነት መከባበር እንዳለባቸው አመልክቷል።

በተለይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የቤተሰብና ሀገር አደራ ስላለብን አዎንታዊ ሚና በመጫወት ለሌለው መልካም አርአያ መሆን ይገባል ብሏል።

ለዚህ ደግሞ የተማሪዎች ኅብረት ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማትጋር ተቀናጅቶ እንደሚሰራ አስታውቋል።

ዩኒቨርስቲ ትንሿን ኢትዮጵያ የማይባት ሥፍራ ስለሆነች ለእኔ ልዩ ፍቅር ይሰማኛል ያለችው ደግሞ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዝዳንት ተማሪ ሃና ነገሠ ናት።

ይህም በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ አንድም ጊዜ የፀረ ሰላም ኃይሎች ተልዕኮ ማስፈጸሚያ ሆና እንደማታውቅ ትናገራለች።

ሀገሪቱ የሰው ዘር መገኛ፣ የጠበብት መፍለቂያ፣ የታላቁ የዓባይ ወንዝ ባለቤት ልጆች ሆና ሳለ ስንዋደድ እንጂ ስንጋጭ አያምርብንም ያለችው ሃና ትምህርት ሲጀመር ከመጡበት ዓላማ ውጭ ለሁከት መጋለጥ እንደማይገባ አስተያየቷን ሰጥታለች።

ችግር ቢያጋጥም እንኳን በውይይት ለመፍታት መጣር እንደሚገባም ጠቁማለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም