ሥልጠናው ወቅቱን የሚመጥን የአመራርነት ቁመና እንዲኖራቸው ያመቻቸ መሆኑን የሲዳማ ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ሥልጠናው ወቅቱን የሚመጥን የአመራርነት ቁመና እንዲኖራቸው ያመቻቸ መሆኑን የሲዳማ ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ
ሐዋሳ፣ ነሐሴ 29/2012 (ኢዜአ) እየተሰጣቸው ያለው ሥልጠና ወቅቱን የሚመጥን የአመራርነት ቁመና እንዲኖራቸው ያመቻቸ መሆኑን የሲዳማ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ።
በክልሉ በተዘጋጀው ሥልጠና እየተሳተፉ ካሉት አመራሮች መካከል አቶ ተሰማ ዲማ በተለይ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው እንደ ሀገር ለማሳካት ባታቀዱ ትልሞችና ሊያጋጥሙ በሚችሉ ፈተናዎች ዙሪያ ሰፊ ውይይት ማካሄዳቸውን ተናግረዋል።
በዚህም የተሟላ የአመራር ቁመና እንዲኖራቸው ያመቻቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ በመነሳት እንደ አንድ አመራር ተፅዕኖዎችን ተቋቁመው የለውጡን ጉዞ ለማሳካት የክልሉን ሕዝቦች ባሳተፈ መልኩ ለመሥራት እንደተዘጋጁ አስታውቀዋል።
አቶ አክሊሉ ዓለሙ በበኩላቸው በአመራሩ ዘንድ ካሁን በፊት የነበሩ የአመለካከትና የተግባር ልዩነትን ለይቶ በማረም የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማሳካት የሚያስችል ቁመና እንዲይዝ ሥልጠናው ጠቃሚ ሆኖ እንዳገኙት ተናግረዋል።
በየደረጃው የሚገኘው አመራር ሊያጋጥሙ የሚችሉ መሰናክሎችን ተጋግዞ መወጣት እንዳለበት ሥልጠናው አቅጣጫ ማመላከቱን ገልጸው በሕዝቦች መካከል ወንድማማችነትን የማጠናከር ጉልህ ሚና ሊኖረው እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የሀገሪቱን ህልውና በማስጠበቅ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሊከበሩ ይገባል ያሉት አስተያየት ሰጪው በዚህ ረገድ ይህንን ለማስፈጸም ጠንካራ አመራር እንዲሆኑ ሥልጠናው አቅም እንደሆናቸው ተናግረዋል።
ሲዳማ አዲስ ክልል እንደመሆኑ ሥልጠናው አመራሩ በለውጡ እሳቤዎችና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ የሀሳብና የተግባር አንድነት እንዲፈጠር ከፍተኛ እገዛ ማድረጉን የገለጹት ደግሞ ሌላው አመራር ወይዘሮ እመቤት ኢሣያስ ናቸው።
በውጪም ሆነ ሀገር ውስጥ ያሉ የኢትዮጵያ ጠላቶች በተለያዩ መንገዶች ተፅዕኖ ለመፍጠር እየሰሩ እንደሆነ የተናገሩት ወይዘሮ እመቤት "ይህን ጫና ለመቋቋም ውስጣዊ አንድነታችንን ለማጠናከር ሥልጠናው ገንቢ ሚና አለው" ብለዋል።
ከሥልጠናው ባገኙት ግንዛቤ መሠረት የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ከራሳችን ባለፈ ከሌሎች ክልሎች አመራሮች ጋር አንድነት በመፍጠር የፓርቲውን ራዕይ ልናሳካ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
ቀጥሎ ባለው የአቅም ግንባታ ሥልጠና በክልል፣ ማዕከልና ወረዳ አስተባባሪ ደረጃ የሚገኙ 421 አመራሮች እየተሳተፉ መሆኑን ቀደም ብሎ ተገልጿል።