በህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር የተጠረጠሩ ተያዙ - ኢዜአ አማርኛ
በህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር የተጠረጠሩ ተያዙ

ደሴ፣ ነሐሴ 29/12 (ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦ ወረዳ በህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር የተጠረጠሩ ሶስት ግለሰቦችን መያዙን ፖሊስ አስታወቀ።
የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ሰይድ አብዱ ለኢዜአ እንደገለጹት ግለሰቦቹ የተያዙት ከትናንት በስትያ ቀትር ላይ ነው።
ግለሰቦቹ ሁለት ሺህ 359 የክላሽንኮቭ ጥይትና 101 የጥይት መያዥ ካዝና በህገወጥ መንገድ ከአፋር ጭፍራ ወረዳ ወደ ደቡብ ወሎ ቢስቲማ ከተማ ለማስገባት ሲሞክሩ በአራባቲ ኬላ ፍተሻ ተይዘዋል።
የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ-3 74585 አአ በሆነ አይሱዙ የጭነት ተሽከርከሪ ጥይትና ካዝናውን በመደበቅ በመጓዝ ላይ እንዳሉ መያዛቸውን ተናግረዋል።
ጥይትና ካዝናውን ሲያጓጉዙ የነበሩ አሽከርካሪውን ጨምሮ ሶስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።
"የፀጥታ ኃይሉ ከተጠርጣሪዎቹ ለቀረበላቸው የመደለያ ገንዘብ ሳይሸነፉ ግለሰቦቹን በመያዝ ሙያዊ ግዴታቸውን በመወጣት ለሀገርና ለህዝባቸው ያላቸውን ታማኝነት አረጋግጠዋል" ብለዋቀል።
ግለሰቦቹን ለህግ ለማቅረብ ጉዳዩ በምርመራ ላይ መሆኑን ዋና ኢንስፔክተር ሰይድ አብዱ አስታውቀዋል።