ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፈጠራ ቴክኖሎጂዎችን ለእይታ አቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፈጠራ ቴክኖሎጂዎችን ለእይታ አቀረበ
ጎንደር ነሐሴ 28/2012(ኢዜአ) ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚረዱ 17 የፈጠራ ቴክኖሎጂዎችን ለእይታ ማቅረቡን አስታወቀ፡፡
በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መምህራንና ተማሪዎች የተሰሩት የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎች በተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ዛሬ ተጎብኝቷል፡፡
"አውቶማቲክ ሴንሰር" የተገጠመለትን የእጅ ማስታጠቢያ የፈጠራ ስራ ያቀረበው የዩኒቨርሲቲው የኤሌክትሪካል ኢኒጂነርኒግ መምህር ታደለ መለሰ ናቸው፡፡
የእጅ ማስታጠቢያው የአለም ጤና ድርጅት ያወጣውን መስፈርት በማሟላት በየ20 ሴኮንዱ ፈሳሽ ሳሙናን በመጠቀም እጅ ማስታጠብ የሚያስችል ቴክኖሎጂ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የፈጠራ ቴክኖሎጂው ኤሌክትሪክ በሌለባቸው አካባቢዎች በፀሐይ ኃይል በሚሞላ ባትሪ ጭምር የሚሰራና ከእጅ ንክኪ ነጻ እንደሆነም አስረድተዋል።
በኮሮና ምክንያት በጽኑ ህክምና ክፍል ተኝተው ለሚታከሙ ህሙማን የመተንፈሻ "መካኒካል ቬንትሌተር "በራሱ ፈጠራና ዲዛይን ቴክኖሎጂውን የሰራው ደግሞ የኤሌክትሮ መካኒካል ተማሪው ጌታቸው አለሙ ነው፡፡
ቴክኖሎጂው በተገጠመለት የሞባይል መተግበሪያ በመታገዝ ህመምተኛ የሚከታተለው ሃኪም የትም ቦታ ሆኖ አተነፋፈስና የመሳሪያውን ደህንነት መከታተል የሚያስችለው እንደሆነም ተናግሯል፡፡
የፈጠራ እውቀቱንና ክህሎቱን በመጠቀም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አንድ ተጨማሪ "መካኒካል ቬንትሌተር "በማምረት ለዩኒቨርሲቲው ሆስፒታል ለመሰጠት ማቀዱንም ገልጿል፡፡
ምግብና መድኃኒትን ከአንድ የህክምና ህንጻ ወደ ሌላ ህንጻ በቀላሉና በፍጥነት ማድረስ የሚያስችል ድሮን /በራሪ አካል/ የፈጠራ ቴክኖሎጂም በእለቱ ለእይታ ቀርቧል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የኢንጂነሪንግ ኢንስቲትዩት ከተሰሩ ተጨማሪ የፈጠራ ቴክኖሎጂዎች መካከልም ሙሉ በሙሉ ፊትን መሸፈን የሚያስችል የፕላስቲከ ጭንብል፣ ለእጅ ንክኪ የማያጋልጡ የበርና መስኮት መክፈቻ እጀታዎች ይገኙበታል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቢኒያም ጫቅሌ በበኩላቸው የቴክኖሎጂ ፈጠራዎቹ ሆስፒታሉ ያለበትን የመተንፈሻ "መካኒካል ቬንትሌተር" እጥረት የሚያቃልሉ በመሆናቸው በፍጥነት ወደ ምርት እንዲሸጋገሩ ይደረጋል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው የፈጠራ ቴክኖሎጂዎቹን ወደ ምርት ለማሸጋገር የሚያስችለውን የማምረቻ ኢንተርፕራይዝ ለማቋቋም እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናገሩት ደግሞ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶክተር አስራት አፀደወይን ናቸው፡፡
በተለይም "አውቶማቲክ ሴንሰር "የተገጠመላቸውንና ከእጅን ንክኪ ነጻ የሆኑ የእጅ መታጠቢያ ቴክኖሎጂዎች በብዛት ተመርተው ስራ ላይ እንዲውሉ መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡
ዶክተር አስራት እንዳሉተ ዩኒቨርሲቲው ኮሮናን ለመከላከል እንዲረዳ ከአንድ ሚሊዮን 600ሺህ ብር በላይ በመመደብ ሃገር በቀል እውቀትን መሰረት ያደረጉ 11 የጥናትና ምርምር ስራዎች እያካሄደ ይገኛል።
ጎንደር ዩኒቨርስቲ በ2013 የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት መጀመሩንም አመልክተዋል።