ቀጥታ፡

በአማራ ክልል በዘመን መለወጫ በዓል አለአግባብ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር እየተሰራ ነው

ባህር ዳር ነሐሴ 28/2012(ኢዜአ) በአማራ ክልል የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ በገበያ አለአግባብ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ከወዲሁ ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ። 

በበዓሉ  ምክንያት  የዋጋ ጭማሪ እንዳይከሰት በባህር ዳር ከተማ ከነጋዴዎች ጋር ዛሬ ውይይት ተካሄዷል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ተዋቸው ወርቁ በውይይቱ ወቅት እንዳሉት ለዘመን መለወጫ በዓል መሰረታዊ ሸቀጦችን በተቻለ አቅም ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ ነው።

የዘመን መለወጫ በዓሉ ኃይማኖትና ባህል ሳይለይ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የሚያከብረውና እንደየአቅሙ አስፈላጊ ሸቀጦችን የሚገዛበት  ወቅት ነው ብለዋል።

ከበዓሉ ጋር ተያይዞ የፍጆታ ምርቶች እጥረት እንዳይፈጠርና የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ለመከላከል በየደረጃው ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አቶ ተዋቸው አስታውቀዋል።

በዓሉን ታሳቢ በማድረግም  ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ 18 ሚሊዮን ሊትር ዘይትና 104 ሺህ ኩንታል ስኳር መቅረቡን ጠቅሰዋል።

እስካሁንም ከ14 ሚሊዮን ሊትር በላይ ዘይትና 95 ሺህ ኩንታል ስኳር ለተጠቃሚው ህብረተሰቡ መሰራጨቱን አመልክተው ቀሪውም በመከፋፈል ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

መሰረታዊ ሸቀጦችን በመደበቅ በህብረተሰቡ ላይ አለአግባብ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ ህገ ወጥ ነጋዴዎችን ለመከላከልም የተቋቋመው ግብረ ኃይል እየሰራ ነው ብለዋል።

ሌሎች ህብረተሰቡ በብዛት የሚፈልጋቸው ሽንኩርት፣ ቅቤና የእርድ እንስሳት በሸማቹ ፍላጎት ልክ በትስስር ለመቅረብ  ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

ነጋዴው በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በሸማቹ ህብረተሰብ ላይ የተፈጠረውን ጫና  ከግምት ያስገባ ግብይት ሊያካሂድ እንደሚገባም  የቢሮው ምክትል ኃላፊው  አሳስበዋል።

ከዚህ ውጭ በሸቀጦች ላይ አለአግባብ  ዋጋ ጨምሮና ምርት ደብቆ በተገኘ ነጋዴ ላይ  ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም አስታውቀዋል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ አቶ ታደሰ ይርዳው በበኩላቸው ምክር ቤቱ በነጋዴውንና ሸማቹ ማህበረሰብ መካከል ጤናማ ግንኙነት እንዲኖር እየሰራ ነው ብለዋል።

በተለይም አለአግባብ  የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉና ምርት የሚደብቁ ነጋዴዎችን ለሚመለከተው የመንግስት አካል ጥቆማ በመስጠት እርምጃ እንዲወሰድባቸው የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

በንግድ ሱቆች ላይ በየጊዜው የሚደረግ የኪራይ ጭማሪ ነጋዴው ለዋጋ ጭማሪ እንዲያደርግ እያስገድደው ነው ያሉት ደግሞ በባህር ዳር ከተማ በአትክልትና  ፍራፍሬ ንግድ የተሰማሩት አቶ ይበልጣል እምቢያለ ናቸው።

በተለይም የሽንኩርት ምርት በክልሉ አርሶ አደሮች ተመርቶ እየቀረበ ባለመሆኑ የትራንስፖርት ወጭ ዋጋው እንዲጨምር እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት የሽንኩርት ዋጋ እየጨመረ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም የአቅርቦት እጥረት ሳይሆን ምርቱ ከሌላ አካባቢ  እየቀረበ በመሆኑ ነው ብለዋል።

በውይይት መድረኩ  የንግዱ ማህበረሰብ ፣ የመንግስትና ንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አመራሮች   ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም