ብዝሀ ህይወት በአግባቡ ጥበቃ ካልተደረገለት የከፋ ጉዳት ሊያመጣ እንደሚችል ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
ብዝሀ ህይወት በአግባቡ ጥበቃ ካልተደረገለት የከፋ ጉዳት ሊያመጣ እንደሚችል ተጠቆመ
አዲስ አበባ ነሀሴ 28/2012 (ኢዜአ) ብዝሀ ህይወት በአግባቡ ጥበቃ ካልተደረገለት ጉዳቱ የከፋ ሊሆን እንደሚችል የብዝሀ ህይወትና አየር ንብረት ለውጥ ፎረም አስታወቀ።
የብዝሀ ህይወትና አየር ንብረት ለውጥ ፎረም በመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ ስርአተ ምህዳር የአካባቢ ጥበቃ ችግሮች ላይ በዘርፉ ጥናት ካደረጉ ባለሙያዎች ጋር ዛሬ ተወያይቷል።
የኢትዮጵያ የስነ ህይወት ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ቢቂላ ወርቅነህ በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ የብዝሀ ህይወት ጥበቃን ዘላቂ በማድረግ ህብረተሰቡ በአካባቢና በተፈጥሮ ሀብት ላይ የሚኖረውን ግንዛቤ ማሳደግ ይገባል።
የመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ ስርአተ ምህዳር በብዝሀ ህይወት የታደለ ቢሆንም የህዝብ ቁጥር እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ በርካታ ደኖች ተጨፍጭፈዋል።
በዚህም ከፍተኛ የአፈር መሸርሸር መፈጠሩን ነው የጠቆሙት።
"የታችኛው የመሬት ክፍል አሸዋ በመልበሱ የግብርና ምርት እንዲቀንስና የግጦሽ መሬትም እንዲመናመን አድርጓል" ብለዋል።
በተለያዩ ቦታዎች የሚገነቡ ኢንዱስትሪዎች በርካታ ጥቅሞች ቢኖራቸውም የሚለቋቸው ኬሚካሎች የአካባቢ ስነህይወትን እየጎዳ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
"በካይ ኬሚካሎቹ ወደ ከባቢ አየር በመግባት በሰዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የጤና ችግርም እያስከተሉ ይገኛል" ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት የሚስተዋሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ከተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ጋር በቀጥታ የሚገናኙ መሆናቸውንም ነው አቶ በቂላ የተናገሩት ።
አክለውም ፎረሙ በአሁኑ ወቅት በአካባቢው የተከሰተውን የብዝሀ ህይወት መመናመን ለመታደግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባዮሎጂካል ሶሳይቲ ኦፍ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ጥናቶችን እያደረገ ይገኛል።
በቀጣይም እነዚህን ጥናቶች ይፋ በማድረግ ለፖሊስ ግብአት መሆን በሚችሉበት መንገድ እንደሚዘጋጁም ጠቁመዋል።
ምሁራንም በቅንጅት በመስራት የተደቀነውን አደጋ ለመቀልበስ ሌት ተቀን መስራት እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት።
አቶ በቂላ እንዳሉት በተለያየ መንገድ የተጎዳውን መሬት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እንዲያገግም ፎረሙ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ የሚመለከታቸው አካላት እየተጎዳ ስላለው የመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ ስርአተ ምህዳር ትኩረት እንዲሰጡ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል ።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው መንግስት በአሁኑ ወቅት ለብዝሀ ህይወት የሰጠው ትኩረት ጥሩ መሆኑን ጠቁመው፣ በቀጣይም ዘርፉን የማሳደግ ሥራ መጠናከር እንዳለበት ተናግረዋል።
የብዝሃ ህይወት ጥበቃ ሥራዎችን የዘርፉ ባለሙያዎች ቢመሩት አመርቂ ውጤት ሊገኝ እንደሚችልም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የብዝሃ ህይወትና አየር ንብረት ለውጥ ፎረም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2004 የአየር ለውጥ ፎረም ተብሎ ቢቋቋምም በሂደት በአካባቢ እና በብዝሀ ህይወት ጥበቃ ላይ እየሰራ ይገኛል።