አዲስ ዓመትን ተከትሎ የአትክልትም ሆነ የመሰረታዊ ሸቀጦች አቅርቦት እጥረት አይኖርም - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ ዓመትን ተከትሎ የአትክልትም ሆነ የመሰረታዊ ሸቀጦች አቅርቦት እጥረት አይኖርም
አዲስ አበባ ነሀሴ 28/2012 (ኢዜአ)አዲስ ዓመትን ተከትሎ የአትክልትም ሆነ የሌሎች መሰረታዊ ሸቀጦች የአቅርቦት እጥረት እንደማይኖር የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ከንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተወጣጣ ቡድን በመዲናዋ የአትክልትና ፍራፍሬ እንደሁም የመሰረታዊ ሸቀጥ አቅርቦትን በተመለከተ በተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
የልኡካን ቡድኑ በጉብኝቱ የስኳር አቅርቦትን ጨምሮ የአትክልት ፍራፍሬ እንዲሁም የሌሎች ፍጆታዎች አቅርቦት የተሟላ መሆኑን አረጋግጧል።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኮሙንኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ እንዳሉት በአዲስ ዓመት የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ሌሎች የፍጆታ እቃዎእች እጥረት እንዳይኖር ከወዲሁ ተሰርቷል።
ከበዓሉ ጋር ተያይዞ የአትክልትና ፍራፍሬ እጥረት እንዳይኖር በሁሉም መደብሮች በቂ አቅርቦት መኖሩንም ጠቁመዋል፡፡
የግብይት ሰንሰለቱ ጤናማ እንዲሆን እና የምርት መደበቅም ይሁን መሰወር እንዳይኖር ከህብረተሰቡ ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የመሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ከፍተኛ ፋላጎት እንደሚኖር በማሰብም ከዘመን መለወጫ በዓል ቀደም ብሎ ፍልጎትን መሠረት ያደረገ የአቅርቦት ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
በመንግስት በኩል አንዳንድ መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ ተመቻችቷል ያሉት አቶ ወንድሙ በዚህም በዘይት እና ሌሎች ምርቶች ላይ ከፍተኛ ቅናሽ መታየቱን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የአቅርቦት ክትትልና ዌር ሃውሲንግ ቡድን መሪ አቶ ደሣለኝ ተሠማ እንዳሉትም አሁን ላይ በቂ ሊባል የሚችል የስኳር አቅርቦት አለ።
ከውጪ ገበያ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ግዢ ተፈፅሞ እስካሁን 900 ሺህ ኩንታሉ አገር ውስጥ ገብቶ በመጋዘን የሚገኝ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
ቀሪው ስኳርም በመጓጓዝ ላይ በመሆኑ በቅርቡ አገር ውስጥ የሚገባ መሆኑን ተናግረዋል።
በጉብኝቱ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነጋዴዎች እንዳሉት የባእሉን መቃረብ ተከትሎ ምንም አይነት የምርት እጥረት የለም።
በየመጋዘኖቻቸውም ሆነ በገበያው ላይ በቂ ምርት መኖሩንም ተናግረዋለ።
በስፍራው ያገኘናቸው ሸማቾች በበኩላቸው ምርት በበቂ ሁኔታ ቢኖርም በአንዳንድ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን ገልጸውልናል።
የዘንድሮው የኢትዮጵያ አዲስ አመት (የዘመን መለወጫ በዓል) የፊታችን አርብ የሚከበር ይሆናለ።