ቀጥታ፡

የመድሃኒት እጥረት ለህክምና አገልግሎት ማነቆ ሆኖብናል … የጤና ተቋማት

አዲስ አበባ ነሀሴ 28/2012 (ኢዜአ) የመድሃኒትና የህክምና መገልገያዎች አቅርቦት እጥረት በህክምና አገልግሎት ላይ  ማነቆ መሆኑን የጤና ተቋማት ገለጹ።

የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የመድሃኒቶች፣የህክምናመገልገያዎችናየላብራቶሪ ሪኤጀንቶችን እንዲገዛላቸው በጠየቁት መጠን እያቀረበላቸው   አለመሆኑን የጤና ተቋማት ቅሬታ አቀረቡ፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ የህክምና ግብአቶችን የሚያቀርበው ኤጀንሲ  መድሀኒቶችን  በበቂ መጠን ባለማቅረቡ የጤና ተቋማት አገልግሎትን  በማስተጓጎሉ  መንግስት  አማራጮችን   ተግባራዊ እንዲያደርግ  ጠይቀዋል።

 የኤጀንሲው የህክምና ግብአት አቅርቦት ለስራቸው ላይ ፈተና መሆኑን   ለኢዜአ ካስረዱ የጤና ተቋማት መካከል የአበበ ቢቂላ ጤና ጣቢያ አንዱ ነው ፡፡

የጤና ጣቢያው ሀላፊ አቶ ብርሃኑ በዳዳ እንዳሉት በኤጀንሲው በኩል እንዲቀርብላቸው ከሚጠይቁት የመድሃኒት፣የህክምና መገልገያዎችና የላብራቶሪ ሪኤጀንቶች መካከል እየቀረበ ያለው መጠን አነስተኛ ነው።

በጤና ተቋሙ መጥፋት የሌለባቸው መድሃኒቶችና የህክምና ግብአት  ጭምር እጥረት በመኖሩ ከሌሎች ተቋማት  ለመዋስ የሚገደዱባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።

በአብነትም በቅርቡ ኤጀንሲው እንዲገዛላቸው ከተጠየቁት 210 የመድሃኒትና የህክምና መገልገያዎች 35 አይነትን ብቻ ማቅረቡን ተናግረዋል።

ይህም  ጤና ጣቢያው ለህብረተሰቡ በሚሰጠው አገልግሎት ላይ  ተጽዕኖ ማሳደሩን ሀላፊው ገልጸዋል ።

በቅርቡ ጤና ጣቢያው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት የተጀመረ በመሆኑ በበቂ መጠን ከኤጀንሲው መድሃኒት ማግኘት ካልተቻለ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ቅሬታ ይፈጥራል ሲሉም አክለዋል።

ከኤጀንሲው መድሃኒቶች በማይገኘበት ወቅት  በጨረታ  ለመግዛት ጊዜ ይፈጃል የሚሉት አቶ ብርሃኑ መንግስት ችግሩን  ለመፍታት ሌሎች አማራጮች  እንዲፈልግ ጠይቀዋል፡፡

የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የፋርማሲ ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ ሂርኮ በበኩላቸው የኤጀንሲው  አቅርቦት ላይ መሻሻል የነበረ ሲሆን በቅርብ ጊዜ ውስጥ ግን የአቅርቦት እጥረት ችግር እየገጠማቸው መሆኑን ይናገራሉ።

በኤጀንሲው እየቀረበ ያለው የመድሃኒቶች፣የህክምና መገልገያዎችና የላብራቶሪ ሪኤጀንቶች    መጠን አነስተኛ መሆኑን ነው የገለጹት።

ኤጀንሲው ላይ ከፍተኛ ጫና ያለ በመሆኑ በመንግስት በኩል ድጋፍ ሊደረግ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ወይዘሮ አድና በሬ በበኩላቸው የመድሃኒቶች፣የህክምና መገልገያዎችና የላብራቶሪ ሪኤጀንቶች የአቅርቦት ክፍተት እንዲፈጠር የሚያደርጉ ችግሮች መኖራቸውን ተናግረዋል።  

የአገር ውስጥ የመድሃኒት አምራቾች በሚፈለገው ልክ አለማቅረብና በአለም አቀፍ ደረጃ በሚወጡ ጨረታዎች  አንዳንድ መድሃኒቶችን በበቂ ሁኔታ አምራቾች አለማቅረባቸው የእጥረቱ መነሻ መሆናቸውን በምክንያት ጠቅሰዋል፡፡

የአገር ውስጥ አምራቾች 1 ነጥብ 1 ቢሊዬን ብር ዋጋ ያላቸው 102 አይነት መድሃኒቶች እንዲያቀርቡ የግዢ ትዕዛዝ ተጠይቆ  ማቅረብ የቻሉት ግን በአማካይ 20 በመቶ ብቻ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል።

ይህን ችግር በሚያጋጥምበት ወቅት በድጋሚ የሚወጣ የግዢ ጨረታ ጊዜ በሚወስዱ  ክፍተት እንደሚፈጠር አስረድተዋል።

መንግስት የአገር ውስጥ አምራቾቹን አቅርቦትን ለማሳደግ የ30 በመቶ ቅድሚያ ከፍያና ብድር ማመቻቸቱን  አስረድተዋል።

የህክምና ግብአቶች አቅራቢዎች  አፈጻጸምን በመለካት የሚያበረታታበትና የማያሻሽሉትንም    ከአቅራቢዎች ዝርዝር ውስጥ  መሰረዛቸውን  ተናግረዋል።

አነሰተኛ አቅራቢ ያላቸው መድሃኒቶች ላይ በተደጋጋሚ ጨረታ በማውጣት የሚባክነውን ጊዜ ለመቀነስ የማዕቀፍ ግዢ ስርዓት ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል።

የኤጀንሲው አቅርቦት ከጤና ተቋማት የግዢ ፍላጎት ጋር የተመጣጠነ ለማድረግም  ተቋማት በየሳምንቱ  ያላቸውን የመድሃኒት አቅርቦት መረጃ ለኤጀንሲው ሪፖርት እንዲያደርጉ  መሰራቱን ዳይሬክተሯ አንሰተዋል።

ይሁን እንጂ በአገሪቱ ከኮቪድ 19 መከሰት ጋር ውይይቶች መቀዛቀዛቸው የመረጃዎች ክፍተት በመፈጠሩና በአንዳንድ አካላትም በንቃት ያለመሳተፍ ክፍተቶችን ለመሙላት  እየተሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ  1 ሺህ 373 አይነት መድሃኒቶችን፣ የህክምና መገልገያዎችንና መሳሪያዎችንና የላብራቶሪ ሪኤጀንቶችን ለጤና ተቋማት ያቀርባል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም