ቀጥታ፡

አዲሱን ዓመት ጥላቻን በማስወገድ በአብሮነትና በመልካም ተግባራት መቀበል ይገባል

አዲስ አበባ ነሀሴ 28/2012 (ኢዜአ) መጪውን አዲስ ዓመት ዜጎች በመቻቻል፣ በአብሮነትና ጥላቻን በማስወገድ እንዲቀበሉና ለአገራዊ አንድነት እንዲተባበሩ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ጥሪ አቀረበች።


ቤተክርስቲያኗ አዲሱን የ2013 ዓመት መምጣት ተከትሎ የእንኳን አደረሳችሁና የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፋለች።

የቤተክርስቲያኗ ምክትል ፕሬዚዳንት ቄስ ዶክተር ኪሮስ ላቀው እየተጠናቀቀ ባለው ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ በጎም መጥፎም ነገሮች ተስተውለው እንደነበር አስታውሰዋል።

በዓመቱ ስኬታማ ልማቶች፣ በርካታ አዳዲስና ተስፋ ሰጪ ነገሮች የታዩበት ቢሆንም በአንጻሩ እጅግ አስከፊ ሁኔታዎች የተከሰቱበት እንደነበር አስታውሰዋል።

በተለይ የእርስ በእርስ ግጭቶች፣ አለመተማመንና የዜጎች ህይወትና ንብረት መጥፋት ጨምሮ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የተከሰተበት መሆኑን ተናግረዋል።

በእዚህም የብዙሃን ህይወት መናጋቱ ደግሞ ሁኔታዎችን እጅግ አሳሳቢ አድርጎ እንደነበር ቄስ ዶክተር ኪሮስ  ገልጸዋል።

"ይሁን እንጂ አሮጌው ዓመት እየተገባደደና አዲሱ ዓመት እየመጣ በመሆኑ ህዝበ ክርስቲያኑ የ2013 ዓመትን በአዲስ ተስፋና በመልካም እሳቤ ሊቀበል ይገባል" ብለዋል።

ለዚህም ጥላቻን በማስወገድ በመቻቻል፣ በአብሮነትና በአዲስ መንፈስ ህይወትን መጀመር አስፈላጊ መሆኑን ቄስ ኪሮስ አመልክተው፣ ልብን ንጹህ ማድረግና ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

ችግሮች እንዲፈቱ መንግስት ከማህበረሰቡ፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከተለያዩ አካላት ጋር ሰላማዊ ውይይቶችን በማድረግ ዘላቂ መፍትሄ ማበጀት እንዳለበትም ነው የገለጹት

ቤተክርስቲያኗም አልፎ አልፎ እርስ በርስ እየተስተዋለ ያለውን አለመግባባትና ልዩነቶች ለመፍታት አበክራ እንደምትሰራም አረጋግጠዋል።

በሌላ በኩል እየተገባደደ ባለው ዓመት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የመጀመሪያ ምዕራፍ ውሃ ሙሌት ሥራ መከናወኑ የአገሪቱን ህዝቦች ከጫፍ ጫፍ አንድ ማድረጉና ቤተክርስቲያኗንም እንዳስደሰተ ቄስ ዶክተር ኪሮስ ገልጸዋል።

"የታችኛው ተፋሰስ አገራት በግድቡ ዙሪያ እንቅፋት በመሆን እንዳይሳካ ለማድረግ የተለያዩ ስልቶችን ቢጠቀሙም ኢትዮጵያ እጅ አለመስጠቷ የህዝቦቿን ጥንካሬ ያሳያል" ሲሉም ቄስ ዶክተር አክለዋል።

በሕዳሴው ግድብ የሚስተዋለውን አብሮነትና መተጋገዝ በሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ላይም በማጉላት እየተሸረሸረ ያለውን የዜጎች አንድነት ወደ ቀድሞ መመለስ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ቤተክርስቲያኗ የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እያበረከተች ያለውን አስተዋጽኦ አሁንም ከመንግስትና ከህዝብ ጋር በመሆን አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።

ለዚህም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የቤተክርስቲያኗ አባላት ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የቤተክርስቲያኗ ምክትል ፕሬዚዳንት ቄስ ዶክተር ኪሮስ አክለውም መጪው አዲስ ዓመት በዓለም ህዝቦች ዘንድ ስጋት የደቀነው የኮቪድ-19 በሽታ የሚጠፋበትና ክትባት የሚገኝበት እንዲሆን መልካም ምኞት ተመኝተዋል።

የሕዳሴ ግድብ ከፍጻሜው የሚደርስበት፣ በዜጎች መካከል ጠብ፣ ጥላቻና መቃቃር የሚወገድበትና አብሮነት የሚነግስበትም እንዲሆንም እንዲሁ ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም