በከባድ ዝናብ የሚጎዱ መንገዶችን ለመጠገን ኅብረተሰቡና መስተዳድሮች ሊተባበሩ ይገባል...የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን - ኢዜአ አማርኛ
በከባድ ዝናብ የሚጎዱ መንገዶችን ለመጠገን ኅብረተሰቡና መስተዳድሮች ሊተባበሩ ይገባል...የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 28/2012(ኢዜአ) በከባድ ዝናብ የሚጎዱ መንገዶችን በአፋጣኝ ለመጠገን ኅብረተሰቡና መስተዳድሮች ሊተባበሩ እንደሚገባ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አሳሰበ።
በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች በሚጥለው ከባድ ዝናብ ምክንያትየተወሰኑ መንገዶች በጎርፍ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑንም ገልጿል።
የባለስልጣኑ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ለኢዜአ እንዳሉት በ2012 በጀት ዓመት በ653 ሚሊዮን ብር ወጪ ከ10 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ ተጠግኗል።
ይሁንና ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ በመኖሩ የተወሰኑ መንገዶችና ድልድዮች ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
ለከፍተኛ ጎርፍ የተጋለጡት መንገዶችና ድልድዮች በትራንስፖርት ፍሰቱ ላይ መስተጓጎል እንዳይፈጥሩ ባለስልጣኑ እየተከታተለ ጥገና እንደሚያደርግም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ስር የነበሩ 10 የመንገድ ጥገና ቅርንጫፎች ወደ ባለስልጣኑ በመካተታቸው የጥገና ሂደቱን ለማሳለጥ አግዞናልም ብለዋል አቶ ሳምሶን።
በክረምቱ ዝናብ ሳቢያ ችግሩ ከተከሰተባቸው አካባቢዎች መካከል የአደሌ ግራዋ - ቡታጅራ ጉብሬ ወደ ሀረር መስመር ጮሌ- ባሳሪያና ድባጤ መስመሮች ጥገና እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የአካባቢው ማኅበረሰብ፣ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚያደርጉት እገዛ መልካም ቢሆንም አሁንም ውስንነቶች እንደሚታዩ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ለመንገድ ጥገና የሚያስፈልጉ አፈርና ድንጋይ ለባለስልጣኑ ማቅረብ እንዳለባቸው በሕግ ቢደነገግም አንዳንዶቹ ከፈቃድ ጋር በተያያዘ 'ቢሮክራሲ ያበዛሉ' ብለዋል።
በክረምቱ ዝናብ ሳቢያ በመሬት መንሸራተት የተዘጉና በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች የተጎዱ መንገዶች በፍጥነት ተጠግነው መደበኛ አግልግሎት እንዲሰጡ ሊተባበሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በኅብረተሰቡ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ብሎም በኢኮኖሚ ላይ ሊደርስ የሚችለውን መስተጓጎል ለመከላከል በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግም አክለዋል።
የመንገድ ጥገና ስራ የባለስልጣኑ ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ትብብር የሚጠይቅ መሆኑን መገንዘብ ይገባል ያሉት አቶ ሳምሶን አልፎ አልፎ በመስተዳድሮችም ሆነ በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚታየው ቸልተኝነት ተገቢ አለመሆኑን አመልክተዋል።