ማዕከሉ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ግብረ ኃይል አቋቁሜ እየሰራሁ ነው አለ - ኢዜአ አማርኛ
ማዕከሉ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ግብረ ኃይል አቋቁሜ እየሰራሁ ነው አለ
አዲስ አበባ ነሀሴ 28/2012 (ኢዜአ)የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል ግብረ ኃይል አቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን የሸዋሮቢት ማረሚያ ማዕከል ገለጸ።
የኮሮና ቫይረስ ዓለም አቀፍ ስጋት ከሆነ ሰነባብቷል፤ እያሳደረ ያለው ተጽዕኖም እያየለ ነው።
ቫይረሱን ለመከላከል የጥንቃቄ ስራዎች ከሚከናወኑባቸው ተቋማት መካከል ማረሚያ ቤት አንዱ ነው።
ከማረሚያ ቤቶች መካከል ኢዜአ በሸዋሮቢት በመገኘት እየተወሰዱ ያሉትን የጥንቃዌ እርምጃዎች ተመልክቷል።
የማረሚያ ማዕከሉ ዳይሬክተር ኮማንደር አቡ ግርማ በማዕከሉ ያለው የታራሚዎች ብዛት ቫይረሱን ለመላከል የተጠናከረ እንቅስቃሴ እንደሚያስፈልግ አመላካች ነው ይላሉ።
ቫይረሱ መድኃኒት የሌለውና የሚያስከትለውን አደጋ ክብደት ከግምት ውስጥ በማስገባት ለአባሎችና ታራሚዎች ግንዛቤ ማሳደጊያ ተግባራት ተከናውነዋል።
በማዕከሉ ጭምብል መልበስ፣ርቀት መጠበቅና የእጅ ንጽህናን መጠበቅ ግዴታ መሆኑን መተማመን ላይ መደረሱንም አብራርተዋል።
በተለይም በታራሚዎችና በአባሎች መካከል ቅርርብ እንዳይኖር ተደርጓል ያሉት ኮማንደር አቡ፣ ለጉዳይ ወደ ውጭ የወጣ ታራሚ ሲመለስ ግዴታ ጭምብል ለብሶና ታጥቦ እንዲገባ የሚያስገድድ መመሪያ እንደሚተገበር አክለዋል።
ከቃሊቲና ቂሊንጦ የሚመጡ ታራሚዎች ወደ ማረሚያ ቤቱን ከመቀላቀላቸው በፊት ለ14 ቀናት የሚቆዩበት ቦታ መዘጋጀቱንም አስረድተዋል።
ከዚህ ውጭ የማረሚያ ቤቱ አባሎች ጭምብል ማጥለቃቸውንና ርቀት መጠበቃቸውን የሚከታተል ግብረ ኃይል መቋቋሙን ነው የተናገሩት።
ማዕከሉ በባለሙያዎች የፊት ጭምብል እያመረተ መሆኑን ነው ኮማንደር አቡ ገልጸዋል።
በዚህም ማዕከሉ የራሱን የጭምብል ፍላጎት ከሟማላት ባለፈ ለሸዋሮቢት ከተማ፣ለአማራ ክልል ፖሊስና ፌዴራል ፖሊስ አባላት ድጋፍ እያደረግን ነው ብለዋል።