ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች በትግራይ ለውጥ እንዲመጣ እገዛ ሊያደርጉ ይገባል ... ትዴፓ - ኢዜአ አማርኛ
ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች በትግራይ ለውጥ እንዲመጣ እገዛ ሊያደርጉ ይገባል ... ትዴፓ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 27/2012(ኢዜአ) የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) በትግራይ ለውጥ ለማምጣትና ሕዝቡን ከችግር ለማዳን መሰረታቸውን ሌሎች ክልሎች ላይ ያደረጉ የፖለቲካ ድርጅቶች እገዛ ያስፈልጋል ብሏል።
የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ሥራአስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግዴና መድሕን ለኢዜአ እንደተናገሩት "የትግራይ ሕዝብ በጭቆናና አስከፊ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል"።
''ላለፉት 30 ዓመታት የትግራይ ሕዝብ ያረፈበት ቀን የለም፤ ትግል ላይ ነው የቆየው'' ሲሉም ተናግረዋል።
"አሁንም ሕዝቡ በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ውስጥ ባሉ ግለሰቦች የሚደርስበትን አፈና እየተቃወመ ይገኛል" ነው ያሉት።
ባለፉት ቀናትም በሽሬ፣ በእንትጮ፣ በአድዋና በሌሎች ከተሞች የለውጥ ጥያቄ ያነገቡ መልዕክቶች ሲተላለፉ እንደነበር ኃላፊው ገልጸዋል።
በትግራይ ሰላም ሲኖር የኢትዮጵያ ሰላም የሚረጋገጥ መሆኑን በመረዳት ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶችም እገዛ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል ኃላፊው።
''ኢትዮጵያ ሰላም እንድትሆንና ዴሞክራሲና ማህበራዊ ፍትህ እንዲሰፍንባት ሁሉም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድነት መታገል አለባቸው" ብለዋል።
"አክቲስቶች፣ ፖለቲከኞችና ምሁራን የትግራይን ሕዝብ በሚመለከት የሚሰነዝሯቸው ግዴለሽ አስተያየቶች በተለይ ወጣቱን እያስከፉ በመሆኑ ጥንቃቄ ያስፈልጋል" ሲሉም ተናግረዋል።
የመገናኛ ብዙሃንም እንዲሁ ሥራቸውን ኃላፊነት በተሞላበት መልኩ እንዲያከናውኑ ጠይቀዋል።