ቀጥታ፡

አመራሮቹ ለ"ገበታ ለሃገር" ፕሮጀክት የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለመለገስ ወሰኑ

ሀዋሳ፣ ነሐሴ 27/2012 (ኢዜአ) የደቡብ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ለ"ገበታ ለሃገር" ፕሮጀክት ድጋፍ እንዲውል የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለመለገስ ወሰኑ።

እነዚህ ከ550 በላይ አመራሮች የወሰኑት በሀዋሳ ከተማ በስልጠና ላይ እያሉ ነው። 

ከአመራሮቹ መካከል የጌዴኦ ዞን የፓርቲው ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ጸሐይ ወራሳ በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት ሀገሪቱ  ከለውጥ ማግስት አንስቶ ታላቁ የኢትዮጵያ ሃዳሴ ግድብ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት፣ የአንድነት፣ እንጦጦና ሸገር ታላላቅ ፕሮጀክቶች የመፈጸም ብቃት እንዳለት በተግባር እየታየ ነው።

ይህ ደግሞ በሃገር ደረጃ ሰፍቶ እስከ ታች ድረስ በመውረድ በየአከባቢው ያለውን አቅም በማስፋት የህዝቡን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ የብልጽግና ትልም ነው ያሉት ወይዘሮ ጸሐይ ከግብ ለማድረስ መደጋገፍ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እሳቸውም የአንድ ወር ደመወዛቸውን በፈቃዳቸው ሲለግሱ ታሪካዊ አሻራቸው ለማሳረፍ አስበው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ሃገሪቱ የጀመረቻቸው ፕሮጀክቶች ካላት ተፈጥሮዊና ሰው ሠራሽ አቅም በመነሳት የፓርቲውን ግብ ብልጽግናን ለማሳካት ትክክለኛ መንገድ ነው ያሉት ደግሞ የስልጤ ዞን የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አቶ አሊ ከድር ናቸው፡፡

ፕሮጀክቶቹ ሃገራዊ አንድነትን ለማጎልበትም ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወትም ገልጸው ተመሳሳይ ልማቶችን በየአካባቢው ለመስራት መጀመር እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ለአፈጻጸሙ ደመወዝ ከመለገስ ባለፈ ማህበረሰቡን አስተባብረው ሃብት በማሰባሰብ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

የዳውሮ ዞን የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አቶ ተክሌ በዛብህ በበኩላቸው ብልጽግና የሚለው ዕሳቤ በዕውነትና ተግባር የሚያምን በመሆኑ ሠርቶ ማሳየትን ይጠይቃል ብለዋል፡፡

ይህም ከቤተ መንግስት፣ በሸገርና ሌሎች ፕሮጄክቶች አፈጻጸም እንዲሁም የተያዙ ዕቅዶች በተግባር የመግለጽ ማሳያ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በተለይ በደቡብ ኮይሻ የሚሠራው ፕሮጀክት አካባቢውን ውጤታማና ተጠቃሚ ከማድረግ አንጻር የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ እንደሚሆን ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል፡፡

ገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ በሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች ያሉን ሃብቶች ለመጠቀም የሚፈጥረው ዕድል ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው ለስኬታማነቱ የዞኑን ማህበረሰብ በማስተባበር ለመደገፍ እንደሚጥሩ ተናግረዋል፡፡

የየም ልዩ ወረዳ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አቶ ይሁን አሰፋ በለውጥ ሂደት በተግባር የታዩ የልማት ስራዎች ብልጽግና የያዘውን ራዕይ እንደሚፈጸም የሚያሳይ ስለመሆኑ ያመለክታል ብለዋል፡፡

ገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች  በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ለመተግባር በጠቅላይ ሚኒስትር አነሳሽነት መጀመሩ የኢትዮጵያዊያን  አንድነት ለማጠናከርና የኔነት ስሜት ለመፍጠር የጎላ ድርሻ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

በግላቸው ለፕሮጀክቶቹ ስኬታማነት  ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ የማስተባበር ስራ  እንደሚያከናውኑ አብራርተዋል፡፡

የለውጡ አመራር በሃገሪቱ ማነቆ ሆኖ የቆየው የሜጋ ፕሮጀክት አፈጻጸም ላይ እያሳየ ያለው ስኬት አስገራሚና ፓርቲው ግቡን ለማሳካት የሚያስችል አቅምና ብቃት እንዳለው ያሳያል ያሉት የቤንቺ ሸኮ ዞን የፓርቲው ከፍተኛ አቶ ፍቅሬ አማን ናቸው፡፡

ገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች የቱሪዝምና የሥራ ዕድል ማስገኛ ዘርፎችን  ለማነቃቃት ያላቸው ሚና የላቀ መሆኑን ተናግረዋል።

ለፕሮጀክቶቹ ግንባታ ድጋፍ እንዲውል በአመራር ደረጃ በመነጋገር የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለመለገስ መወሰናቸውን ገልጸው ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድ አስተሳሰብ አስተዋጽኦ እንዲያደርግም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም