ቀጥታ፡

የዓለም ባንክ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በቅርበት መስራቱን እንደሚቀጥል ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 27/2012(ኢዜአ) የዓለም ባንክ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በቅርበት መስራቱን እንደሚቀጠል አስታወቀ።

የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ቢሮ በትዊተር ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ባንኩ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በቅርበት መስራቱን ይቀጥላል።

ባንኩ ለኢትዮጵያ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ሙሉ ድጋፍ እንዳለውና ለማሻሻያው የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጿል።

በዓለም ባንክ ግሩፕ ስር በሚገኘው ዓለም አቀፍ የልማት ማህበር "አይ.ዲ.ኤ 19" ለ10 ዓመት የሚቆይ መርሃግብር ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኝ ሲሆን መርሃግብሩ በድህነት የሚገኙና ለአደጋ ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ አገራት ድጋፍ የሚደረግበት ማዕቀፍ ነው።

መርሃግብሩ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ግጭት፣ የአደጋ ተጋላጭነት፣ ጾታ፣ አስተዳደር፣ ቴክኖሎጂና ኢኮኖሚያዊ ሽግግርን ያካተተ ነው።

የ "አይ ዲ ኤ 19" መርሃግብር የመጀመሪያ ትግበራ ዓመት በኢትዮጵያ ለሚከናወኑ የልማት ሥራዎች የፋይናንስ ድጋፍ ማዕቀፍ 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ገደማ መሆኑን የዓለም ባንክ ገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግስት የበጀት ድጋፍን ጨምሮ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ለባንኩ ማስገባቱን አመልክቷል።

የዓለም ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ በጉዳዩ ላይ እንደሚወያይና መደበኛ አሰራርን ተከትሎ ውሳኔ እንደሚሰጥ በዓለም ባንክ ኢትየጵያ ቢሮ የትዊተር ገጽ የሰፈረው መረጃ ያሳያል።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ቢሮን መግለጫ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም