ባለፉት ሶስት ቀናት 329 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ተመለሱ - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ሶስት ቀናት 329 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ተመለሱ
አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 27/2012(ኢዜአ) ከሊባኖስ ባለፉት ሶስት ቀናት 329 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።
ተጨማሪ 74 ኢትዮጵያውያን ዛሬ ወደ አገራቸው ገብተዋል።
ወደ አገራቸው ከገቡት መካከል በእስር ቤት የነበሩ፣ የመኖሪያ ፍቃድ ያልነበራቸው፣ በአሰሪዎቻቸው በደል ደርሶባቸው እርዳታ ሲደረግላቸው ይገኙበታል።
እንዲሁም በሆስፒታል ህክምናዋን እንድትከታተል እገዛ ሲደረግላት የነበረች ኢትዮጵያዊትም እንደምትገኝበት በቤይሩት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
በተመሳሳይ ዛሬ ማታና በመጪዎቹ ቀናት 81 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ገልጿል።
ከሊባኖስ የሚመለሱት ኢትዮጵያውን ወደ አገራቸው የተመለሱት በግለሰቦች፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና ቡድኖች በተደረገላቸው የትራንስፖርት ወጪ የተደረገላቸው ዜጎች ይገኙበታል።
የትራንስፖርት ወጪያቸውን የሸፈኑ ኢትዮጵያውያንም ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድም ለተመላሾቹ የአውሮፕላን ቲኬት ቅናሽ በማድረግ መተባበሩ ይታወቃል።
በጥቅምት 2012 በሊባኖስ ህዝባዊ ተቃውሞ ከተነሳበት ጊዜ አንስቶ በስምንት ዙሮች ከ2 ሺህ 300 በላይ ኢትዮጵያውያን ከሊባኖስ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።
በዘጠነኛ ዙርም 3 ሺህ 300 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ለመመለስ መመዝገባቸውና መረጃዎቻቸው ለሊባኖስ ኢሚግሬሽንና ደህንነት መሥሪያ ቤት መላኩን ጽህፈት ቤቱ ገልጿል።