የፈረንሳይና የኢትዮጵያ ወዳጅነት ማህበር የሕክምና ቁሶቁሶችን ድጋፍ ሊያደርግ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የፈረንሳይና የኢትዮጵያ ወዳጅነት ማህበር የሕክምና ቁሶቁሶችን ድጋፍ ሊያደርግ ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 27/2012(ኢዜአ) የፈረንሳይና የኢትዮጵያ ወዳጅነት ማህበር ከሊዮን ሜትሮፖል ከተማ ጋር በመተባበር ያሰባሰበውን የሕክምና መሳሪያዎችን ለኢትዮጵያ ድጋፍ ሊያደርግ መሆኑ ተገለጸ።
ማህበሩ ከሊዮን ሜትሮፖል ከተማ ጋር በመተባበር ግምታቸው ከ35 ሺህ 500 ዩሮ በላይ የሆነ የሕክምና ቁሶችና መሳሪያዎችን ማሰባሰቡን በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ መግለጻቸውን በፓሪስ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።
ድጋፉ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎች፣ የህክምና ጓንቶች እንዲሁም በደም ውስጥ ያለን የኦክስጅን መጠን፣ የልብ ምትና የሰውነት ሙቀትን የሚለኩ መሳሪያዎችን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ለሚከናወኑ ሥራዎች ድጋፉ እንደሚውልም የጠቆሙት አምባሳደር ሄኖክ፤ ድጋፉን ላሰባሰበው የፈረንሳይና የኢትዮጵያ ወዳጅነት ማህበር ምስጋና አቅርበዋል።
"በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እየተስፋፋ መጥቷል፤ ቫይረሱ ዘር፣ የሃይማኖትና የፖለቲካ አመለካከት ሳይለይ ሰዎችንም እየገደለ ነው" ብለዋል።
"ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመታደግ በጋራ እንስራ" ሲሉም አምባሳደሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የሊዮን ሜትሮፖል ከተማ ከአዲስ አበባ ጋር የእሀትማማችነት ከተማ ግንኙነት ያለው ሲሆን፤ ሁለቱ ከተሞች ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ 1999 እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ሁለቱ ከተሞች ባለፈው ህዳር ወር 2012 ዓ.ም ትብብራቸውን ማጠናከር የሚያስችላቸው ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።
የሸገር ፕሮጀክትን ጨምሮ ሌሎች የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ላይ የቴክኒክ እና የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ በስምምነቱ ውስጥ ከተካተቱ ጉዳዩች አንዱ ነው።
ስምምነቱ በአዲስ አበባ ለተጀመረው የተማሪዎች ምገባ መርሃግብር ከሊዮን ሜትሮፖል ከተማ የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ያስችላል።
በከተማ ፕላን እና በትራንስፖርት ዘርፍ ላይ የአቅም ግንባታ ድጋፎችን ማድረግን ስምምነቱ እንደሚያካትትም በወቅቱ መገለጹ የሚታወስ ነው።