ቀጥታ፡

ከኮሮና ራስን ለመጠበቅ ለአፍታም መዘናጋት እንደሌለበት አባ ገዳና የሀገር ሽማግሌዎች አሳሰቡ

ዲላ፣ ነሐሴ 27/2012 (ኢዜአ) ህብረተሰቡ ከኮሮና ቫይረስ ራስን ለመጠበቅ ሊደረጉ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች ለአፍታም ቢሆን መዘናጋት እንደሌለበት የጌዴኦ አባ ገዳ እና የሀገር ሽማግሌዎች አሳሰቡ።

አባ ገዳ  ዳንቦቢ ማሮ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሉ በ"ፋጩኤ "ስነ ስርዓት መሰረት ለፈጣሪ ፀሎት ሲያደርሱ  መቆየታቸውን  ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ እራሱን ከወረርሽኙ እንዲጠብቅ ትምህርት ሲሰጠው ቢቆይም ክልከላ ዎችን ከማክበር ረገድ መዘናጋት ሲስተዋል መታዘባቸውን አመልክተዋል።

በተለይ የአፍና አፍንጫ ጭንብል አለመጠቀም፣ በገበያ ቦታዎች የጥንቃቄ ጉድለት፣ በትራንስፖርት እንቅስቃሴ ወቅት የተቀመጡ ክልከላዎችን ያለማክበር  ሁኔታን ጠቅሰዋል።

ለራስና ለሌላውም ህይወት በማሰብ ህብረተሰቡ ከኮሮና ቫይረስ ራስን ለመጠበቅ ሊደረጉ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች ለአፍታም ቢሆን መዘናጋት አይገባውም ብለዋል።

ከመንግስት በኩል በሽታውን ለመከላከል የተቀመጡ አቅጣጫዎችን በተገቢው ተግባራዊ ማድረግም እንዲሁ።

በአካባቢው የሃገር ሽማግሌ የሆኑት ሃይቻ አለማየሁ ህርቤ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት ወረርሽኙ እያሰጋ በመምጣቱ ከቸልተኝነት ፈጥኖ መላቀቅ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በሽታው እንዲጠፋ ታዋቂ ሰዎች የጥንቃቄ መልዕክቶችን ተግባራዊ በማድረግ ለህብረተሰቡ አርአያ ልንሆን ይገባል ብለዋል።

በሽታውን ለመከላከል በመንግስት የተጀመረው የንቅናቄ ዘመቻው እንዲሳካ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ሌላው የሀገር ሽማግሌ አቶ ካሱ ሚኒዶ "እኛ እራሳችንን እየጠበቅን ሌሎች እራሳቸውን እንዲጠብቁ ካላስተማርን የቫይረሱ መስፋፋት የሚያደርሰው ጉዳት የሁሉንም ቤት ያንኳኳል" ብለዋል።

ህብረተሰቡ ርቀቱን እንዲጠብቅ፣ ጭንብል እንዲያደርግ፣ እጆቹን በተደጋጋሚ ጊዜ እንዲታጠብ ትምህርት ቢሰጥም ተግባራዊ በማድረጉ ረገድ ቸልተኝነቱ በዝቷል ሲሉ ገልጸዋል።

የቫይረስ ስርጭት ተባብሶ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል ህብረተሰቡ ቸልተኝነትና መዘናጋቱን ትቶ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባል ፣ የዞኑ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዩሐንስ አሰፋ የወረርሽኙ ስርጭት የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ በህዝብ ዘንድ ተሰሚነት ካላቸው ሰዎች ጋር በመቀናጀት ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም