በኮቪድ-19 ተፅዕኖ የተጎዱ የቱሪዝም ዘርፍ ተዋናዮችን ለማገዝ ያለመ የኦንላይን ፎቶ ኤግዚቢሸን ሊደረግ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኮቪድ-19 ተፅዕኖ የተጎዱ የቱሪዝም ዘርፍ ተዋናዮችን ለማገዝ ያለመ የኦንላይን ፎቶ ኤግዚቢሸን ሊደረግ ነው
አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 27/2012(ኢዜአ) ኮቪድ-19 ተፅዕኖ የተጎዱ የቱሪዝም ዘርፍ ተዋናዮችን ለማገዝ ያለመ 'የኦንላይን ፎቶ ኤግዚቢሸን ተግባራዊ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ሆቴልና ማርኬቲንግ ማህበር ገለፀ።
ማህበሩ ወደ አፍሪካ የሚገቡ የውጭ ቱሪስቶች ኢትዮጵያን መዳረሻ ለሚያደርጉ 'የቱሪስት ፓኬጅ'ም እያዘጋጀሁ ነው ብሏል።
የማኅበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታዲዎስ ክንፉ ለኢዜአ እንደተናገሩት ኑሮአቸውን ጎብኚዎችን በማስተናገድ ብቻ ያደረጉ የቱሪስት መዳረሻዎች አሁን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ ''በእጅጉ'' ተጎድተዋል።
በዚህም ማህበሩ የዘርፉ ተዋናዮች ከደረሰባቸው ጉዳት እንዲያገግሙ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂና ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴሮች ጋር በመተባበር የኦንላይን ኤግዚቢሽን ለማዘጋጀት እየሰራ ነው ብለዋል።
ኤግዚቢሽኑን ለማድረግ የሚያስችለው መተግበሪያም 80 በመቶው ሥራው መጠናቀቁን የገለጹት አቶ ታዲዎስ፤ ለአንድ ዓመት የሚቆየው መተግበሪያ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ክፍያውን በመፈጸም ኤግዚቢሽኑን የሚሳተፉበት ሥርዓት መሆኑን ገልጸዋል።
ማህበሩ ባደረገው ጥናት በኤግዚቢሽኑ ከ70 ሚሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱን አስረድተዋል።
ገቢውም ለመሰረተ ልማት ዝርጋታና ተጎጂዎች ከጉዳታቸው እንዲያገግሙ ድጋፍ ለማድረግ ያለመ እንደሆነም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋዕ።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ተፈጥራዊም ሆነ በባህላዊ የመስህብ ሃብቶቿ ቱሪስቶችን ለመሳብ ዕምቅ አቅም እንዳላት ገልጸው፤ ዘርፉን በማስተዋወቅ ረገድ ውስንነት በመኖሩ ተጠቃሚ እንዳልሆነች አመልክተዋል።
በዚህም አፍሪካን በየዓመቱ ከሚረግጡ ከ25 ሚሊየን በላይ የውጭ ቱሪስቶች ውስጥ ኢትዮጵያን የሚጎበኙት አንድ ሚሊዮን አይሞሉም ተብሏል።
ማህበሩም ምሥራቅ አፍሪካን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ኢትዮጵያንም የሚጎበኙበትን 'የቱሪስት ፓኬጅ' የተሰኘ አሰራር እያዘጋጀ መሆኑንና ስራውም 70 በመቶ መጠናቀቁንም ገልጸዋል።
በዚህም በተለይም ኬንያን፣ ታንዛኒያንና ደቡብ አፍሪካን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ኢትዮጵያንም የሚጎበኙበት አጋጣሚ እንደሚፈጠር ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ በመሰራት ላይ የሚገኙ የቱሪዝም ልማት ሥራዎችም ለቱሪስቶች ቆይታ ተጨማሪ ዕድል እንደሚፈጥርላቸው አቶ ታዲዎስ ተናግረዋል።