ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ስፖርት ቤተሰቦች ለተቸገሩ ተማሪዎች 20 ሺህ ጫማዎችን ለመለገስ ቃል ገቡ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 27/2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ስፖርቱ ቤተሰቦች በአዲስ አበባ ከተማ በችግር ውስጥ ለሚገኙ 20 ሺህ ተማሪዎች ጫማ ለማልበስ ቃል ገቡ።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስፖርት እንቅስቃሴ አስተዋጽኦ ላደሬጉ ዕውቅና ተሰጥቷል።

ቤተሰቦቹ ድጋፉን ለማድረግ ቃል የገቡት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጋር  ትናንት ምሽት  ባደረጉት የትውውቅና የቃል ኪዳን መድረክ ላይ ነው።

በመድረኩ በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ 36 የስፖርት ማህበራትና ፌደሬሽኖች ከአስተዳደሩ የቀረበውን “ለአንድ ተማሪ አንድ ጫማ” ጥሪ ለማሳካት ተስማምተዋል።

በዚህም  ስምንት ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ለማበርከት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

በቀጣይነትም አስተዳደሩ በሚያደርጋቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት ላይ ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የስፖርት ቤተሰቦቹ አስተዳደሩ ያቀረበውን ጥሪውን በመቀበል ለሰጡት ምላሽ ምስጋና አቅርበዋል።

''ከተባበርንና አብረን ከቆምን የማናልፈው አንዳች ፈተና የለም''ብለዋል። 

 ስፖርት ለአንድ አገር ዕድገት ፣ አብሮነትና ሰላም መሰረት መሆኑን ገልጸው፣የከተማዋን የማስ ስፖርት መርሐ ግብር እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በመድረኩ በአስተዳደሩ ስፖርት እንቅስቃሴ የላቀ ሚና ላበረከቱ ሶስት ግለሰቦችና ሁለት ተቋማት ዕውቅና ሰጥቷል።

እውቅና የተሰጣቸው ግለሰቦች የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የበላይ ጠባቂ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ፕሬዚዳንት አቶ አብነት ገብረመስቀልና የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ፕሬዚዳንት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ናቸው።

 በተቋማት ደረጃ  የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ዕውቅና አግኝተዋል።

በመድረኩ ላይ የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክ ፌደሬሽን፣ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አመራሮችና አትሌቶች ተገኝተዋል።

መድረኩን ያሰናዱት የስፖርት ማህበራትና የአዲስ አበባ ከተማ አሰተዳደር ስፖርት ኮሚሽን ጋር በመተባበር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም