በኢትዮጵያ የግብርና ምርት እድገት በእርሻ መሬት መስፋፋት ከሚታየው ለውጥ ባለፈ ምርታማነቱም ጨምሯል

1767

አዲስ አበባ ሃምሌ 6/2010 በኢትዮጵያ የግብርና ምርት በእርሻ መሬት መስፋፋት ከሚታየው ለውጥ ባለፈ ምርታማነቱም በተጨባጭ እየተሻሻለ መምጣቱን የግብርናና እንስሳት ሃብት ሚኒስቴር ገለጸ።

ግብርናው ኢኮኖሚውን በማሳደግ የዜጎችን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እንዲችልም በመላ ሀገሪቱ የአፈር ለምነት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል ተብሏል።

“የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት ትንተና” በሚል ርዕሰ ጉዳይ እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር ከ 1995 እስከ 2010 የተደረገው ጥናት እንደሚያመላክተው የግብርና ምርት እድገት የተመዘገበው የእርሻ መሬት መጠንና የሰው ጉልበት ቁጥር በመጨመሩ ነው።

በአገሪቱ በ 1995 የነበረው 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር የእረሻ መሬት በ 2010 ወደ 11 ሚሊዮን ሄክታር በማደጉ የተገኘ የምርት ጭማሪ እንደሆነም ይገልፃል ጥናቱ።

በተመሳሳይ በግብርና ምርት ላይ የተሰማራው የሰው ኃይል ከ 40 እስከ 50 በመቶ ማሻቀቡ የግብርና ምርቱን ተፈጥሯዊ እድገት እንዲያመዝን አድርጎታል ይላል ጥናቱ።

የግብርናና እንስሳት ሃብት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማዬሁ ብርሃኑ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ጥናቱ የኢትዮጵያ ግብርና ምርት ምርታማነት እንዲሻሻል ከመፈለግ የመጣ ቀናኢ አስተሳሰብ ቢሆንም ተጨባጭ ለውጦች እንዳሉ መዘንጋት የለበትም።

ነገር ግን የምርቱ መጠን እንደሰብሎቹ ዓይነት የሚለያይ ሆኖ የአፈር ለምነቱ አሁን ያለውን በአማካኝ በሄክታር 39 ኩንታል ምርት ወደ 60 ኩንታል ማሳደግ ይችላል ብለዋል።

በምርትና ምርታማነት አመካይነት በኢኮኖሚ እድገቱ ያበረከተው አስተዋፅኦ እንዳለ ሆኖ የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥና ለኢንዱስትሪው በቂ ግብዓት ለማቅረብ በምርምር የተደገፉ የግብርና ስራዎችን በማከናወን በኩል አሁንም ውስንነት አለ ብለዋል።

በ 1983 ዓ.ም ከ50 ሚሊዮን ኩንታል የማይበልጠው የአገሪቱ የግብርና ምርት በአሁኑ ወቅት 316 ኩንታል የደረሰው በእርሻ መሬት መስፋፋት ብቻ ሳይሆን ምርታማነቱም በተጨማጭ ለውጥ በማስመዘገቡ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የእርሻ መሬት በአማካኝ ከ 50 እስከ 60 ኩንታል በሄክታር ማምረት የሚያስችል ቢሆንም በስፋት ከሚመረቱት ሰብሎች መካከል ስንዴ በአማካኝ 27 በቆሎ 39 ኩንታል በሄክታር ነው የሚገኘው።

እነዚህን ለአርሶ አደሩ የሚቀርቡ የማዳበሪያና ምርጥ ዘር ግብዓቶች ከእርሻ መሬቱ ጋር ተስማሚ መሆናቸውን የሚያሳይ የአፈር ለምነት ፍኖተ ካርታ በመላ ሀገሪቱ ተዘጋጅቷል ብለዋል አቶ አለማዬሁ።

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ባለው 14 ሚሊዮን ሄክታር የእርሻ መሬት ከ 17 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች በማምረት ስራ እንደሚሳተፉ የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።