በየትኛውም አውደ-ውጊያ በአሸናፊነት ለመወጣት በሁሉም ወታደራዊ መስክ ብቃት ያለው የሰው ሃይል ያስፈልጋል ... ጄነራል አደም መሀመድ

94

 አዲስ አበባ ነሐሴ 24/2012 (ኢዜአ) ''በየትኛውም አውደ-ውጊያ የሚያጋጥሙንን ስጋቶች ለመመከትና በአሸናፊነት ለመወጣት በሁሉም ወታደራዊ መስክ ብቃት ያለው የሰው ሃይል ያስፈልጋል'' ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄነራል አደም መሀመድ ገለጹ።

የመከላከያ ሠራዊቱ አባላት በኢንጂነሪንግ፣ በህክምናና ሌሎች ወታደራዊ የሙያ ዘርፎች ከመሰልጠንም ብቃት ያላቸውና ተወዳዳሪ መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ በኢንጂነሪንግና ጤና ሳይንስ ዘርፎች በማስተርስ፣ በመጀመሪያ ዲግሪና በደረጃ 4 ያሰለጠናቸውን 502 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄነራል አደም መሀመድ እንደገለጹት፤ የመከላከያ ሠራዊቱን ለማዘመን ብቃት ያለው የተማረ የሰው ኃይል መፍጠር ይገባል።

ሀገርና ህዝብን ከማንኛውም ጥቃት የሚጠብቅ፣ ግዳጁን በብቃት የሚወጣ ሠራዊት ለመገንባት ለውጡን የሚመጥን ተቋማዊ አደረጃጀት እየፈጠርን ነው ብለዋል።

የመከላከያ ዩኒቨርሲቲም ሠራዊቱን ለማዘመን በሚያደርገው ጥረት የተማረና የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።

''በአዲሱ የመከላከያ ሠራዊት የግንባታ ስትራቴጂ ሠራዊቱ የሀገርና የህዝብ ሃብት እንደሆነ በግልጽ ተቀምጧል'' ብለዋል ጄነራል አደም።

በመሆኑም የመከላከያ ሠራዊቱ አባላት ከማንኛውም የኃይማኖትም ሆነ የፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ በመሆን ሀገራዊና ተቋማዊ ግዳጃቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ዓለምን የቀየሩ የጥናትና ምርምር ውጤቶች እና ሳይንሳዊ ግኝቶች የተመዘገቡት በወታደራዊ ተቋማት መሆኑን አስታውሰው፤ ዩኒቨርሲቲው ለሚያደርገው የጥናትና ምርምር ሥራዎች እገዛ እንደሚደረግለት ተናግረዋል።

መመረቅና የሙያ ባለቤት መሆን የሚያስደስት ቢሆንም፣ ብቻውን ውጤታማ ስለማያደርግ እንደ መነሻ በማድረግ ሀገርን ለማገልገል መጣር እንደሚገባ ገልጸዋል።

የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ ተወካይ ብርጋዴር ጄነራል ዳዊት ወልደሰንበት በበኩላቸው፣ ዩኒቨርሲቲው ብቁና የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራትና የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመበት ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ 10 ሺህ የሚጠጉ ባለሙያዎችን ከሰርተፊኬት እስከ ማስተርስ ዲግሪ አሰልጥኖ ማስመረቁ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም