ከተጎራባች ክልሎች ጋር በመናበብ ከ11 ሺህ ሔክታር በላይ መሬትን ከአንበጣ ተከላክለናል

172

መቀሌ /ኢዜአ/ነሀሴ 24/2012 ዓ.ም የአንበጣ መንጋን ለመከላከል ከተጎራባች ክልሎች ጋር በተናበበ መልኩ እየተሰራ መሆኑን የትግራይ ክልል ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የትግራይ ክልል ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ሀላፊ ዶክተር አትንኩት መዝገቡ የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል እየተደረገ ያለውን ጥረት አስመልክተው ትላንት እንደገለጹት ከአማራና አፋር ተጎራባች አካባቢዎች ጋር በተደረገ ፈጣን የመረጃ ልውውጥ ውጤታማ ስራ ተሰርቷል።

በዚህም በክልሉ 11 ሺህ 200 ሄክታር ሰብል ላይ አጋጥሞ የነበረውን የአንበጣ መንጋ በህብረተሰቡ ተሰታፎ መከላከል መቻሉን ተናግረዋል።

በመጀመሪያ ዙር የመጣውን የአንበጣ መንጋ በተነበበና በተቀናጀ መንገድ መከላከል መዋል ቢቻልም አሁንም በተጠንቀቅ መቆም የሚጠይቅ ወቅት መሆኑን ተናግረዋል። 

የአንበጣ መንጋው የክልሉ ምስራቃዊ ክፍል በሆኑ ሶስት ዞኖች በሚገኙ 12 ወረዳዎች ስር 50 ቀበሌ ገበሬ ማህበራት መከሰቱንም አስረድተዋል።

መንጋው ባለፈው አመት ካጋጠመው በ500 እጥፍ የገዘፈ ቢሆንም በሰብል ላይ የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት በባህላዊና በኬሚካል ርጭት መካለከል መቻሉን ዶክተር አትንኩት ገልጸዋል።

የፌደራል ግብርና ሚኒስቴር የኬሚካል ድጋፍ ከማድረጉ በተጨማሪ የመድሀኒት ርጭቱ በአውሮፕላን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን የቢሮ ሀላፊ ተናግረዋል።

የአንበጣ መንጋም ለመከላከል እየተደረገ ያለውን ጥረት በተያዘው መልኩ ከቀጠለም የመከሩ አዝመራ ከሌሎች አመታት በተሻለ ቁመና እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በ2012/13 ዓ.ም የምርት ዘመን 1ነጥብ2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ በተለያዩ የአዝርእት አይነቶች መሸፈኑንም የቢሮ ሀላፊው ገልጸዋል።

በቢሮው የእፅዋት፣ፀረ-ነፍሳትና ኳረንታይን መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር አቶ መብራህቶም ገብረኪዳን በበኩላቸው መንጋውን በባህላዊ መንገድ ለመከላከል ከተደረገው ጥረት በተጨማሪ 9ሺህ ሊትር ኬሚካል አገልግሎት ላይ መዋሉን ገልጸዋል።

ቀጣይ ይመጣል ተብሎ ለተተነበየው የአንበጣ መንጋም ከ11ሺህ ሊትር በላይ ኬሚካል መዘጋጀቱን ገልጸው የአንበጣ መንጋ ከተከሰተ ነሀሴ 12 ቀን ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት በተደረገው ዘመቻ ከ30ሺህ ህዝብ በላይ መሳተፉን ጠቁመዋል።

ማህበራዊ ረዲኤት ትግራይ(ማረት)ጨምሮ በርካታ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ የልማት ድርጅቶች በገንዘባቸው እና በንብረታቸው ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጋቸውንም ጠቅሰዋል።

በራያ ዓዘቦ ወረዳ አዲስ ቅኝት ቀበሌ ሰሙኑን ያጋጠመው የአንበጣ መንጋ ከህብረተሰቡ ጋራ በመሆን ለመከላከል እንደቻሉ የተናገሩት ደግሞ የቀበሌው ነዋሪ አርሶ አደር ለማ ፍቃዱ ናቸው።

የካራዓ ዲሻቡ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ብርሀነ አለነ በበኩላቸው እንደገለጹት የአንበጣ መንጋ በባህላዊ መንገድ በመከላከል ሰብላቸው ከጥቃት ለማዳን መቻላቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም