ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ እንቦጭን በዘላቂነት በሚያስወግድ ምርምር ላይ ማተኮር አለበት...ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ

117

ባሕርዳር፣ ነሐሴ 23/2012 (ኢዜአ) ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ያለውን የቴክኖሎጂ አቅም ተጠቅሞ የእንቦጭ አረምን በዘላቂነት ማስወገድ የሚችል ምርምር ላይ ማተኮር እንዳለበት የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ አሳሰቡ።

ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን ዛሬ ባስመረቀበት ወቅት የተገኙት ሚኒስትሩ እንዳሉት ባሕርዳር የኒቨርሲቲ በመማር ማስተማር ዘርፍ በሀገሪቱ ከሚገኙ አንጋፋ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል አንዱ ነው።

ዩኒቨርሲቲው በማስተማር በሀገሪቱ የምሁራን እጥረትን በመፍታት ታላቅ ሚና ከማበርከቱም ባለፈ የምርምር ማዕከል ለመሆን እየሰራቸው ያሉ የምርምር ተግባራት የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል።

ኮሮናን ለመከላከል የሚያስችሉ ግብዓቶችን በማምረት በአካባቢው ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዲደርስ በማደረጉም በኩል እንዲሁ።

በጣና ሀይቅ የተከሰተው የእንቦጭ አረም በዘላቂነት ለመከላከል የሚያስችሉ የምርምር ሥራዎችን በማከናወን  የሀይቁን ደህንነት ለመጠበቅ ግንባር ቀደም ሊሆን እንደሚገባው አሳስበዋል።

በተለይም ያለውን ዕውቀትና ክህሎት በመጠቀም ለውጤት የሚበቁ የምርምር ቴክኖሎጂዎችን በማመንጨት የድርሻውን  መወጣት እንዳለበትም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያዊያን የብርሃን ተስፋ የሆነው ታላቁ የሕዳሴ ግድብን ደህንነት ለማስጠበቅ የጣና ሀይቅን መታደግ ለነገ የማይባል የቤት ሥራ እንደሆነም ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

"ሀገር መፍትሔ ፈላጊ ልጆች በሚያስፈልጉባት ወቅት በመመረቃችሁ ዕድለኛ ትውልድ ናችሁ" ያሉት ሚኒስትሩ የኢትዮጵያዊያን የቆየ የመከባበርና መተሳሳብ ባህል በመመለስ ሚናቸውን እንዲወጡም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኝ  በበኩላቸው "ተመራቂዎች በቀሰሙት ዕውቀት ኢትዮጵያን ወደ ነበረችበት የሥልጣኔ ማማ ለመመለስ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል" ብለዋል።

ኢትዮጵያን ለማበልጸግ በሚደረገው ጥረት ተመራቂዎቹ የራሳቸውን አስተዎጽኦ ከማድረግ ባለፈ እንደ ሀገር እየገጠመ ያለው የእርስ በርስ ግጭት ለማስወገድ ከፍተኛ ድርሻ እንደሚጠበቅባቸው አስታውቀዋል።

በዚህ ፈታኝ ወቅት ለመመረቅ የሚያስችሉ መሥፈርቶችን አሟልቶ መገኘት በትምህርት ራስን ለመለወጥ ተግቶ ከሚሰራ አካል የሚጠበቅ ሥራ ነው ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ሀገራዊ የምርምር ሥራ ላይ አተኩሮ እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹት ዶክተር ፍሬው በጣና ሀይቅ ላይ የተከሰተውን እንቦጭ ለመከላከል የሚያስችሉ ምርምሮች እያካሄደ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በመሬት ሀብት አጠቃቀም የሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂ አንተነህ በላይ በሰጠው አስተያየት በተማረበት ሙያ በማገልገል ሀገራዊና ሕዝባዊ ግዴታውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን  ተናግሯል።

የሕክምና ሙያ ዘርንና ሃይማኖትን ሳይለይ ስለሰው ልጅ ሕይወት የሚያጨንቅ በመሆኑ ይህንን ኃላፊነት በተገቢው ለመወጣት እንደምትሰራ የገለጸችው ደግሞ  የሕክምና ሙያ ተመራቂዋ  ቤተልሔም ይትባረክ ናት።

የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ በመደበኛና መደበኛ ባልሆኑ የትምህርት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 7 ሺህ 520 ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል።

በዩኒቨርሲቲው ለረጅም ዓመታት ያገለገሉትና ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የቀድሞው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት የነበሩት ዶክተር ፀሐይ ጀንበሩ የማኅበረሰቡን ችግር ለመፍታት በተለይም በሥነ ትምህርት ዘርፍ ላበረከተቱት አስተዋጽኦ ማስተዋሻ የሚሆን ሐውልት ተመርቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም