የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በሰኔ ወር 30 ሺህ ቶን ምርት አገበያየ

1177

አዲስ አበባ ሀምሌ 5/2010 የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በሰኔ ወር 30 ሺህ ቶን ምርት ማገበያየቱን አስታወቀ።

ምርት ገበያው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ በሰኔ ወር 2010 ዓ.ም 30 ሺህ ቶን ምርት ከ1 ነጥብ 9 ቢሊዮን በላይ ብር በሆነ ገንዘብ አገበያይቷል።

በ20 የግብይት ቀናት ውስጥ 21 ሺህ 374 ቶን ቡና፣ 6 ሺህ 479 ቶን ሰሊጥ፣ 2 ሺህ 285 ቶን ቦሎቄ እንዲሁም 410 ቶን ማሾ ማገበያየቱን በመግለጫው ጠቁሟል።

 ቡና በግብይት መጠኑ 70 በመቶ እንዲሁም በግብይት ዋጋው ደግሞ 82 በመቶ በመያዝ ቀዳሚ ሲሆን ይህ ቁጥር ከግንቦት ወር ጋር ሲነፃፀርም በግብይት መጠን የ27 በመቶ በዋጋ ደግሞ 10 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።

 ይሁን እንጂ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ዓመት ወቅት ጋር ሲነፃፀር በመጠን የ0 ነጥብ 56 በመቶ ቅናሽ ቢያሳይም በግብይት ዋጋ ግን 24 በመቶ ብልጫ አሳይቷል።

 በወሩ 6 ሺህ 749 ሰሊጥ በ297 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ግብይት ሲደረግ ነጭ የሁመራ ሰሊጥ የግብይት መጠኑ 79 በመቶ በዋጋ ደግሞ 80 በመቶ በማስመዝገብ ቀዳሚ ሆኗል።

 2ሺህ 285 ቶን ነጭ ጠፍጣፋና ድቡልቡል ቦለቄ በ35 ሚሊዮን ብር የተሸጠ ሲሆን 410 ቶን አረንጓዴ ማሾ ለግብይት ቀርቦ በ8 ሚሊዮን ብር ተሽጧል።

ይህም ካለፈው ወር አማካኝ ዋጋ ጋር ሲነፃፀር የ33 ነጥብ 5 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።