አመራሮች ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ድጋፍ እንዲውል የወር ደመወዛቸውን ለመለገስ ወሰኑ - ኢዜአ አማርኛ
አመራሮች ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ድጋፍ እንዲውል የወር ደመወዛቸውን ለመለገስ ወሰኑ

ጎንደር፣ ነሐሴ 22/2012 ( ኢዜአ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲና የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አመራሮች ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ድጋፍ እንዲውል የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለመለገስ መወሰናቸው ተገለጸ።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር ወይዘሮ ይዳኙ ማንደፍሮ ለኢዜአ እንደተናገሩት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የልማት ጥሪ ለሀገር ብልጽግናና እድገት ፋይዳው የጎላ በመሆኑ የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮቹ የወር ደመወዛቸውን ለመለገስ በመስማማት ወስነዋል፡፡
ከልማት ጥሪው አንዱ የሆነው የጎርጎራ አካባቢ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ በቅርብ ርቀት የሚገኝ በመሆኑ ሁሉንም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት በቀጣይ ለማሳተፍ የሚያስችል ንቅናቄ ለመፍጠር ኮሚቴ መቋቋሙንም ገልፀዋል።
በተመሳሳይ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የካቢኔ አባላት ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ድጋፍ እንዲውል የወር ደመወዛቸውን ለመለገስ መወሰናቸውን የዞኑ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ አስታውቋል፡፡
የመምሪያው ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ጌታሁን እንዳሉት የወር ደመወዛቸውን ለመስጠት የወሰኑት ከ16 በላይ የዞኑ ካቢኔ አባላት ናቸው፡፡
በዞኑ የምዕራብ ደንቢያ ወረዳ አመራሮችም በተመሳሳይ ሁኔታ የወር ደመወዛቸውን ለመለገስ መወሰናቸውን አቶ ሀብታሙ ጨምረው ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ በአማራ ጎርጎራ ፣ በደቡብና ኦሮሚያም እንደዚሁ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን ለማልማት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል።