ፋሲል ከተማ ለኤርትራ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያቀረበው የወዳጅነት ጨዋታ ተቀባይነት አግኝቷል

80
አዲስ አበባ ሰኔ 5/2010 ፋሲል ከተማ ስፖርት ክለብ ለኤርትራ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያቀረበው የወዳጅነት ጨዋታ ተቀባይነት አገኘ። የኢትዮ-ኤርትራን ግንኙነት ለማጠናከር ፋሲል ከተማ ስፖርት ክለብ ለኤርትራ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በአገሪቷ ፕሪሚየር ሊግ ከሚገኝ ክለብ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል። የኤርትራ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከፋሲል ከተማ ስፖርት ክለብ የቀረበውን ጥያቄ ተቀብሎ ምላሽ መስጠቱን የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ጌታሁን ስዩም ለኢዜአ ገልጸዋል። ፋሲል ከተማ ስፖርት ክለብ የቀረበውን ጥያቄ የኤርትራ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በደስታ በመቀበል የወዳጅነት ጨዋታው በአስመራ እንዲካሄድ መወሰኑን ነው ስራ አስኪያጁ የገለጹት ፌድሬሽኑ በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ጨዋታው የሚካሄድበት ቀንና ፋሲል ከተማ ከማን ጋር እንደሚጫወት ለክለቡ እንደሚያሳውቅ አቶ ጌታሁን ስዩም ተናግረዋል። በአስመራ ከሚካሄደው የወዳጅነት ጨዋታ በተጨማሪ በከተማዋ ጎንደር ፓርክ በሚል የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እንዲሁም የጎንደር የፋሲለደስ የባህል ቡድን ከኤርትራ አቻዎቹ ጋር የባህል ልውውጥ ለማካሄድ እንደታቀደም ጠቁመዋል። በተጨማሪም ፋሲል ከተማ ስፖርት ክለብ ጨዋታውን ከሚያደርገው ክለብ ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት ለማድረግ እቅድ መያዙን ነው አቶ ጌታሁን ያብራሩት። በቀጣይ በአስመራ ለሚካሄደው የቅድመ ዝግጅት ስራ መጀመሩን ጠቅሰው ከደጋፊዎች፣የመንግስት ባለስልጣናት፣ጋዜጠኞችና ሌሎች አካላት ወደ ስፍራው እንዲያቀኑ አስፈላጊው ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም