ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ ላይ የወሰዱት እርምጃ የጀግና ውሳኔ ነው-ምሁራን

113
አዲስ አበባ ሐምሌ 5/2010 በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ለዓመታት የዘለቀው አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ እልባት ማግኘቱ ለቀጠናው አገራት ዓርአያ እንደሚሆን ምሁራን ገለጹ። ምሁራኑ ኬንያ ናይሮቢ ከሚገኘው ኤን.ቲ.ቪ ጋር ባደረጉት ቆይታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በሁለቱ ሀገራት ጉዳይ የወሰዱትን እርምጃ የጀግና ውሳኔ ሲሉ አድንቀውታል። የደቡብ ሱዳን ወጣት መሪዎች ፎረም ሊቀመንበር ዶክተር ፒተር ቢየር አጃክ እንዳሉት፤ በደቡብ ሱዳንና ካርቱም መካከል ያለውን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በር ይከፍታል። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ አዲስ አመራር መጥቶ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የነበረው አለመግባባት ወደ ሰላም እንዲመጣ ላደረጉት የስልጣን ሽግግር ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል። የግጭት አፈታትና ደህንነት ባለሙያ ዶክተር ሙስጠፋ አሊ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ተቋርጦ የነበረው ግንኙነት መጀመሩ ለአፍሪካውያን አንድነት የጎላ ሚና ይኖረዋል ብለዋል። የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር  ማያርዲት እና ተቀናቃኛቸው ዶክተር ሪክ ማቻር ከዚህ ትምህርት ሊወስዱ እንደሚገባም ጠቁመዋል። የቀድሞው የአፍሪካ ህብረት ምክትል ሊቀመንበር አምባሳደር ኢራስተስ ምዌንቻ ለዓመታት የዘለቀው አለመግባባት በሳል በሆነ አመራር የሁለቱን አገራት ወደ ሰላም መልሷል ብለዋል። የመከላከያና የውጭ ፖሊሲ ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ኖህ ሚዳምባ በአፍሪካ በተለያዩ አገሮች መካከል ያለው አለመግባባት መቋጫ አግኝቶ ወደ ልማት ትብብር የሚሸጋገርበት ምዕራፍ ነው ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የኢትዮጵያና ኤርትራ ወንድማማች ህዝቦች ወደ አንድነት እንዲመጡ ያቀረቡት ጥሪ በፕሬዘዳንት ኢሳኢያስ አፈወርቂ ተቀባይነት አግኝቷል። የኤርትራ ከፍተኛ ባለስልጣናት ልዑክ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በኤርትራ አስመራ ይፋዊ የስራ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ በዚህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ተቋርጦ የነበረው የስልክ ግንኙነት እና የወደብ አገልግሎት እንዲጀምር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን መሪዎቹ ገልጸዋል። ኤምባሲዎች በአዲስ አበባና አስመራ ላይ እንዲከፈቱና የሁለቱ ሀገራት አየር መንገዶች ወደ አስመራና አዲስ አበባ በረራ እንዲጀምሩ ውሳኔ ላይ ደርሰዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም