በሸገር ፓርክ የጽዳት ሥራ ለመሳተፍ ከአሜሪካ ሲያትል የመጣው ኢትዮጵያዊ ወጣት

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21/2012 (ኢዜአ) ከአሜሪካ ሲያትል ከተማ መጥቶ በሸገር ፓርክ የጽዳት ሥራ የተሰማራው ኢትዮጵያዊ ወጣት ወንድማገኝ አድማሱ "ባየሁት ነገር ተደንቄያለሁ" ይላል።

አረንጓዴና ንጹሕ አዲስ አበባን በመፍጠር መዲናዋን የከተማ ቱሪዝም መዳረሻ የማድረግ ግዙፍ ዓላማ ያለው የሸገርን ማስዋብ ፕሮጀክት ለመጠናቀቅ ጥቂት ሥራዎች ይቀሩታል።

ፕሮጀክቱ እየተገባደደ ባለበት ሁኔታ በርካታ ቁጥር ያላቸው ጎብኚዎች በየቀኑ መመልከት አግራሞትን ይፈጥራል።

ባልተለመደ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ከታቀደላቸው የጊዜ ገደብ ባነሰና በተስተካከለ ሁኔታ መፈጸም መቻላቸው በፕሮጀክቶቹ እየተሳተፉ ያሉ ባለሙያዎችንም አስደንቋል።

ኢዜአ በሸገር ፓርክ በተለያየ የሥራ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎችን ለማነጋገር በተገኘ ጊዜ በፓርኩ የጽዳት ሥራ ለመሳተፍ ከአሜሪካዋ ሲያትል የመጣን ወጣት አግኝቷል።

ወጣቱ ወንድማገኝ አድማሱ ይባላል፤ ላላፉት 17 ዓመታት ኑሮው በሲያትል ከተማ ነበር።

በአሜሪካ በአንድ የኢንሹራንስ ተቋም ተቀጥሮ ይሰራ እንደነበርና ቤተሰብ ጥየቃም ወደ ኢትዮጵያ ይመላለስ እንደነበር ይናገራል።

በኢትዮጵያ ለውጥ ከመጣ በኋላ ወደ አገር ቤት ገብቶ የራሱን ሥራ ለመሥራት ምቹ ሁኔታ ሲጠብቅ ቆይቷል።

እናም ይህ ወጣት አሁን ከጓደኞቹ ጋር የጽዳት ድርጅት በማቋቋም በሸገር ፓርክ የጽዳት ሥራ ለመሰማራት እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል።

በወሬ የሰማውን በተግባር ማየቱ አግራሞትን የፈጠረበት ወንድማገኝ በአንድ ዓመት ይህን መሥራት ከተቻለ በ10 ዓመት አገሪቷ የት ትደርሳለች የሚለውን መገመት አያዳግትም ይላል።

በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ይህን ትልቅ ፕሮጀክት መጥተው ቢጎበኙ በአገራቸው ለመሥራት ያላቸው ተነሳሽነት ይጨምራል በማለት ገልጾታል።

የፓርኩ የብየዳ ባለሙያ አቶ አሸናፊ ተፈሪ እና የሳይት ሴፍቲ ኢንጂነሩ ዳግማዊ ፍቅሬ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ለዘመኑ የሚመጥን የነገ አሻራ ሥራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዕውቀት ሽግግር፣ ከቱሪዝም፣ ከሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም የአገርን በጎ ገጽታ ከማስተዋወቅ አንጻር ጉልህ ሚና፤ ለአገሪቷ ብልጽግናም አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተናግረዋል።

በሥራው መሳተፋቸውና አሻራቸውን ማኖራቸው የደስታ ስሜት እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።

ወጣት ሣሙዔል እሸቱ እና አብነት ሽመልስ ደግሞ ቦታው ለዘመናት አገልግሎት ሳይሰጥ ታጥሮ መቀመጡንና በቆሻሻና በድንጋይ ካባ የተሞላ እንደነበር ያስታውሳሉ።

አቧራው ተራግፎ የገንዘብ ምንጭ እንዲሆን በመልማቱ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ያነሳሉ።

ከሥራ ዕድል ባሻገርም የወጣቶች እሳቤ እንዲቀየር በማድረግና አዲሱን ትውልድም በበጎ መንገድ ቀርጾ ለማሳደግ ጉልህ ሚና እንደሚኖረውም ተናግረዋል።

ከሁሉ በላይ ደግሞ የተጠናቀቀበት አጭር ጊዜ ለሌሎች ፕሮጀክቶች አስተማሪ መሆኑን፤ ከገንዘብ፣ ከጊዜ፣ ከዕውቀትና ከሥራ ባሕል አንጻርም ልምድ የተወሰደበት ስለመሆኑ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም