በትግራይ ክልል ለአንድ መቶ ሺህ ወጣቶች የአቅም ግንባታ ስልጠና ሊሰጥ ነው

92
መቀሌ ሀምሌ 5/2010 በትግራይ ክልል በክረምት ወራት ለአንድ መቶ ሺህ ወጣቶች ‘‘በፌደራሊዝም ስርዓት ጽንሰ-ሃሳብና ፋይዳው” ላይ ያተኮረ የአቅም ግንባታ ስልጠና እንደሚሰጥ ተገለጸ። በክልሉ በሐምሌና ነሃሴ ወራት በሚሰጠው የአቅም ግንባታ ስልጠና ላይ በክልሉ የሚገኙ የመሰናዶና የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች እንደሚሳተፉ የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አስታውቀዋል። የቢሮው ኃላፊ አቶ ነጋ አሰፋ ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት፣ በፌደራሊዝም ስርዓት ጽንሰ ሃሳብና ፋይዳው ላይ ትኩረት አድርጎ በሚሰጠው የአቅም ግንባታ ስልጠና ላይ 30ሺህ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ይሳተፋሉ። የተቀሩት 70 ሺህ ወጣቶች ደግሞ በክልሉ በሚገኙ የመሰናዶ ትምህርት ቤቶች በመማር ላይ ያሉት መሆናቸውን አመልክተዋል። እንደ ቢሮ ኃላፊው ገለጻ፣ ስልጠናው ወጣቶቹ የፌዴራሊዝም ስርዓት ለኢትዮጰያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የሰጠውን ጥቅም፣ ህገ- መንግስታዊ ስርዓትና የህግ በላይነትን አውቆው እንዲያከብሩና እንዲያስከብሩት ለማድረግ ያለመ ነው። በተጨማሪም የክልሉ ወጣቶች በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ የሚወያዩ ሲሆን፣ በተለይ በኢትዮጵያና በኤርትራ ህዝቦች መካከል የተጀመረው የሰላም ግኑኝነት በሁለቱም ህዝቦች የነቃ ተሳትፎ ከዳር እንዲደርስ ድጋፍ እንዲያደርጉ ለማነሳሳት ጭምር መሆኑን ገልጸዋል። በተያዘው የክረምት ወቅት 30 ሺህ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወጣቶች የሚገኙባቸው 400 ሺህ ወጣቶች በሐምሌና ነሃሴ ወራት በበጎ ፈቃቅ አገልግሎት እንደሚሰማሩ የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ ባለፈው ሳምንት ማስታወቁ ይታወሳል።                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም