በዞኑ 60 ሺህ አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም እርሻ እየተሳተፉ ነው

129

አክሱም፣ ነሐሴ 21/2012 (ኢዜአ) በትግራይ ማዕከላዊ ዞን በተያዘው የመኸር ወቅት 60 ሺህ አርሶ አደሮች በኩታገጠም እርሻ ዘዴ እየተሳተፉ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።

በአስተዳደሩ የአዝርእት ልማት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ኃይለሚካኤል ሓዱሽ ለኢዜአ እንደገለጹት አርሶ አደሮቹ 53 ሺህ ሄክታር በኩታ ገጠም ማሳ በማረስ በጤፍ፣ በበቆሎና በማሽላ ሰብሎች ዘር ሸፍነዋል።


ከኩታ ገጠም ማሳ ውስጥ 40 ሺህ ሄክታሩ በጤፍ ቀሪው ደግሞ በበቆሎና ማሽላ ዘር መሸፈኑን ጠቅሰዋል።

በተለይም በዞኑ በኩታ ገጠም ማሳ የበቆሎና ማሽላ ልማት ሲካሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን የገለጹት ባለሙያው የጤፍ ማሳና የአርሶ አደሮች ቁጥርም በእጥፍ መጨመሩን አመልክተዋል።

ከዚህ ቀደም በኩታገጠም እርሻ ዘዴ በሄክታር በአማካኝ ይገኝ የነበረውን 15 ኩንታል የጤፍ ምርት ወደ 20 ኩንታል ለማሳደግ መታቀዱን ተናግረዋል።

ለተግባራዊነቱም በአንድ ሄክታር ሁለት ኩንታል ማዳበሪያና 10 ኪሎ ግራም ምርጥ ዘር ጥቅም ከላይ እየዋለ መሆኑን ጠቅሰዋል።

“የኩታ ገጠም የእርሻ ልማት አርሶ አደሩ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያግዘው ከመሆኑ በተጨማሪ ትርፍ ምርት ወደ ገበያ ለማቅረብ ይረዳዋል” ብለዋል።

በታሕታይ ማይጨው ወረዳ የከዋኒት ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ገብረሚካኤል አሰፋ ዘንድሮ በኩታ ገጠም እርሻ ሲሳተፉ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን ገልጸዋል።

“የኩታ ገጠም የእርሻ ዘዴ አንድ ዓይነት ሰብል በጋራ በመዝራት በቀላሉ ማሳን ለመንከባከብና ምርት ለመሰብሰብ ያስችላል” ብለዋል።

ባለፈው የምርት ወቅት ከግማሽ ሄክታር ኩታ ገጠም ማሳ ዘጠኝ ኩንታል የጤፍ ምርት በማግኘት ምርታማነትን በእጥፍ ማሳደጋቸውን አስታውሰው ዘንድሮም የተሻለ ምርት ለማግኘት እየተጉ መሆናቸውን አመላክተዋል።

”ኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ ጸረ አረም መድሀኒት ለመርጨትና በሽታን ለመከላከል አመቺ ነው” ያሉት ደግሞ በቆላ ተምቤን ወረዳ የመንጂ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሻባይ አብርሃ ናቸው።

በትግራይ ማዕከላዊ ዞን በ2012/13 መኸር ወቅት በተለያዩ ሰብሎች ዘር ከተሸፈነው 190 ሺህ ሄክታር ማሳ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ከአስተዳደሩ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም