በአምስት ዓመታት ውስጥ የህብረተሰቡን ፍላጎት ለመመለስ መልካም ጅምር ታይቷል – የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ

806

አዲስ አበባ ሀምሌ 5/2010 በአምስት ዓመት ቆይታቸው ህብረተሰቡ በሚፈለግው ልክ ለውጦች ባይመጡም መልካም ጅማሮ የታየባቸው ስራዎች መሰራታቸውን የአዲስ አበባ ምክር ቤት የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎች አባላት ገለጹ።

2ኛው የአዲስ አበባ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ምክር ቤት የመንግስት ወጪና በጀት አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ ዘውዴ ሰኢድ እንዳሉት  “ከፍተኛ ካፒታል ወጪ ወጥቶባቸው የሚገነቡ የመንገድ ግንባታዎች መጓተት ላይ ተጠያቂነት የማስፈን ስራ ተሰርቷል”፡፡

የመንገድ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ወጪ ወጥቶባቸው በተያዘላቸው ጊዜ አለመጠናቀቃቸው ህብረተሰቡ የሚያነሳው ጉዳይ መሆኑንና ይህን በመገንዘብ ቋሚ ኮሚቴው ከከተማው ከንቲባ ጋር የጋራ መድረክ በመፍጠር አፋጣኝ መፍትሄ እንዲያገኝ ጥረት መደረጉን ተናግረዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት ባደረጉት ጥረት አንዳንድ የተጓተቱ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ውል በማቋረጥ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ተደርጓል።

በዋና ኦዲተር የሚቀርቡ ሪፖርቶችና የኦዲት ግኝቶች መነሻ በማድረግ በተለያዩ መስሪያ ቤቶች ያጋጠሙ ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙና በኦዲት ግኝት መሰረት እርምጃ የማይወስዱ ተቋማት የጊዜ ገደብ መቀመጡን ገልጸዋል።

በንብረት ግዥና ንብረት አስተዳደር  ቋሚ ኮሚቴው ክትትል በሚያደርግባቸው ተቋማት አብዛኛዎቹ መመሪያና ህግን ያልተከተለ ግዢ በአምስት ዓመት ቆይታቸው ከተመለከቷቸው ችግሮች በዋነኛነት የሚጠቀስ እንደሆነ አንስተዋል።

ጉዳዩን በተመለከተ በተደጋጋሚ ጊዜ ተቋማቱ ችግሩን እንዲፈቱ ጥያቄ ቢቀርብም የመፍትሔ እርምጃ ከመውሰድ አንጻር ያለው ቁርጠኝነት ዝቅተኛ መሆኑ ትልቁ ፈተና እንደሆነ ወይዘሮ ዘውዴ አስረድተዋል።

የሰው ሃይል እጥረት በቋሚ ኮሚቴው ውስጥ እንዳለና የሰው ሃይል ተጨምሮ በተሻለ መልኩ ቁጥጥርና ክትትል ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ መፈጠር እንዳለበትም ጠቁመዋል።

ምክር ቤቱ በተራዘመለት ተጨማሪ የአንድ ዓመት የቆይታ ጊዜ ቋሚ ኮሚቴው በአገሪቷ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች ከግምት ውስጥ ያስገቡ ስራዎችን ለማከናወን ጥረት እንደሚደረግ አስረድተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የከተማ ልማትና የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ሰላማዊት ወንድምአገኝ ህገወጥ ንግድን በመከላከልና የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ላይ መልካም የሚባሉ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።

በመንገድ ላይ የሚካሄደው ህገ ወጥ ንግድ እንዲቀንስ በንግዱ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ህጋዊ በሆነ መንገድ በመስራት ተጠቃሚ ሊሆኑበት የሚችል አዋጅ መጽደቁን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በህገ ወጥ ንግድ ላይ የተሰማሩ ነዋሪዎች ጊዜያዊ የመሸጫ ቦታ እንዲያገኙ የማድረግ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በአካባቢ ጥበቃ በህብረተሰቡ ጤና ላይ እክል እየፈጠሩ ያለውን የድምጽ ብክለት ተቆጣጥሮ እርምጃ ከመውሰድ አንጻር ጥሩ ስራ መሰራቱን ወይዘሮ ሰለማዊት የተናገሩት።

በቤት ግንባታ መጓተት ላይ በሚፈለገው ደረጃ እንዳይሰራ የአመራር ቁርጠኝነት ማነስና የህብረተሰቡ ችግር ላይ ትኩረት አድርጎ ከመስራት አንጻር ድክመት እንደነበር ገልጸዋል።

የተሰጣቸው ቀጣይ አንድ ዓመት ጊዜ በአገሪቱ እየተካሄዱ ያሉ የለውጥ ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ቅሬታዎች ለመፍታት በትጋት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በአገሪቷ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች በመዲናዋ ደረጃ ፍሬያማ እንዲሆን ከላይ እስከ ታች ያለው የአደረጃጀት መዋቅር በድጋሚ ሊዋቀር እንደሚገባውና አመራሮችም ለአገራዊ እድገት ቅድሚያ በመስጠት በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የማዘጋጃ ቤታዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ተወካይ አቶ ጳውሎስ ደጉ በአምስት ዓመት ቆይታ የመዲናዋ ነዋሪ በዋነኛነት ሲያነሳ የነበረውን የመሬት ጉዳይ ለመፍታት ሰፊ ጥረቶች መደረጋቸውን ተናግረዋል።

በተለይም በመስክ ምልከታ ወቅት ለተለያየ ልማት ፕሮጀክቶች የታጠሩ ቦታዎች ወደ ልማት እንዲገቡ ምክረ ሀሳብ በማስቀመጥ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት የታጠሩ ቦታዎች ወደ ልማት እንዲገቡ መደረጉን ተናግረዋል።

ህገ ወጥ የመሬት ወረራ፣የውሃ ስርጭት ፣በቆሻሻ አጠቃቀምና አወጋገድና የመናፈሻ ፓርኮች ለህብረተሰቡ በስፋት ተደራሽ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ስራዎች ጥሩ በሚባል ሁኔታ መሰራታቸውን አንስተዋል።

የህብረተሰቡን እርካታ በተቻለ አቅም ለማረጋገጥ ቋሚ ኮሚቴው እየሰራ መሆኑንና በቀጣይ ያለውን የአደረጃጀት መዋቀር በማስተካከል ይበልጥ ተደራሽነት ያለው ክትትል ለማድረግ ጥረት ይደረጋል ብለዋል።