በአማራ ክልል 900 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ የአዲስ መንገድ ግንባታና ጥገና ተከናወነ

ባህርዳር ነሐሴ 20/2012 (ኢዜአ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 900 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ የአዲስ መንገድ ግንባታና ጥገና መከናወኑን የአማራ ክልል ገጠር መንገዶች ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት የስራ ሂደት መሪ አቶ ጌትነት ዘውዱ ለኢዜአ እንደገለጹት ለመንገዱ ስራ  የዋለው ገንዘብ የተሸፈነው በክልሉና በፌደራል መንግስት ነው።

በዚህም ተደራሽ ባልሆነባቸው የክልሉ አካባቢዎች 234 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የጠጠር መንገድ  ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱን ተናግረዋል።

ከተገነባው  የጠጠር መንገድ ውስጥ ከዛሪማ- ስንቅ ፣ ከገለጎ-አይከል፣ ከሳህላ-ሰየምት፣ ከሳይንት-ድል፣ ይብዛ - ሰዋሪ፣ ከመካነሰላም- ዋስል የሚያደርስ ይገኝበታል።

የመንገዱ መገንባት  የማህበረሰቡን የልማት  ጥያቄ ለመመለስ ከማገዙም  ባለፈ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ  ክዋኔዎችን በቀላሉ እንዲተገብሩ ማገዙን አቶ ጌትነት አስረድተዋል።

በበጀት ዓመቱ በአገልግሎት ብዛት ተበላሽቶ የነበረ 3ሺህ 464 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ተጠግኖ  ለአገልግሎት መመቻቸቱን አመልክተዋል ።

የጥገና ስራው በጎንደር፣ ወሎ፣ ጎጃምና ሸዋ የመንገድ ጥገና ጽህፈት ቤቶች አማካኝነት እንደተከናወነ አውስተዋል።

እንደ አቶ ጌትነት ገለጻ በመንገዱ ግንባታና ጥገና ሂደት ለ15 ሺህ 670 ሰዎች የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ አድርጓል።

የቋራ ወረዳ ነዋሪ ቄስ ጥበቡ አሻግሬ በሰጡት አስተያየት በአካባቢያቸው ጠጠር መንገድ  ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱን ተናግረዋል ።

የመንገዱ መገንባት አርሶ አደሩም ምርቱን በቀላሉ ወደ ገበያ እንዲያቀርብና ነፍሰጡር እናቶችም ወደ ጤና ተቋማት ሄደው እንዲገላገሉ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።

"ከጥጥራ - ዛጎች የሚወስደው መንገድ በመገንባቱ ለረዥም ጊዜ ስናቀርብ የነበረው ጥያቄ ተመልሶልናል" ያሉት ደግሞ በላይ ጋይንት ወረዳ የቀበሌ አንድ  ነዋሪ አቶ ጌቴ ጥላሁን ናቸው።

"ቀደም ሲል ከጋይንት - ዛጎች ለመድረስ በእግር እስከ 10 ሰዓት ይፈጅ እንደነበር አስታውሰው ፤ አሁን ላይ በትራንስፖርት በአንድ ሰዓት ውስጥ መድረስ  እንደሚችሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም