የሀረሪ ክልል ፖሊሶች ያነሷቸው የጥቅማጥቅም ጥያቄዎች ምላሽ ያገኛሉ...የክልሉ ፍትህና ጸጥታ ቢሮ

59
ሀረር ሐምሌ 5/2010 የሐረሪ ክልል ፍትህና ጸጥታ ቢሮ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት ከመልካም አስተዳደርና ከጥቅማ ጥቅም ጋር ተያይዞ የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ። የቢሮው ኃላፊ አቶ አበበ መብራቱ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ወንጀሎች እንዳይከሰቱ የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ  የፖሊስ አባለቱ ከፍተኛ ስራ እየሰሩ ይገኛሉ። አባላቱ ያሏቸውን ቅሬታዎች በተደጋጋሚ ለቢሮው ባሳወቁት መሰረትም ዛሬ በተካሔደው ውይይት በተለይ ሙስና፣ ፍትሃዊ ያልሆነ ስምሪት፣ የጥቅማጥቅም እጦት እንዲሁም ከማዕረግ አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ያለባቸውን ተጽዕኖ በግልጽ ማሳወቃቸውን ተናግረዋል። በውይይቱም  ችግሩን በሂደት ለመቅረፍ ከአባላቱ ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረው አባላቱ ያካሄዱት ሰላማዊ ውይይት እንጂ የስራ ማቆም አድማ እንዳልሆነም  አስረድተዋል። ያነሷቸው ቅሬታዎች እልባት እስኪያገኙ ድረስም የክልሉን ፖሊስ ኮሚሽን ከምሽነር ስራ ምክትል ኮምሽነሩ ደርበው እንዲሰሩ መደረጉን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅትም በከተማው በሁሉም ስፍራ የክልሉ ፖሊስ አባላት  መደበኛ ስራቸውን እያከናወኑ መሀሆነናቸወውነን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም