በዓሉን አንድነት በሚያጠናክር መልኩ ለማክበር ዝግጅት ተጀምሯል - ፌዴሬሽን ምክር ቤት

93

አዳማ፣ ነሐሴ 19/2012(ኢዜአ) 15ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል አንድነትና ትሥሥርን በሚያጠናክር መልኩ ለማክበር ዝግጅት መጀመሩን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።

አፈጉባዔው በበዓሉ የዝግጅት ምዕራፍና አዘጋገብ ሂደት ላይ ከግልና መንግሥት መገናኛ ብዙሃን ተቋማት ከተወጣጡ አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር ዛሬ በአዳማ ከተማ መክረዋል።

በምክክር መድረኩ አፈጉባዔው እንደገለጹት ባለፉት ዓመታት የተከበሩት በዓላት የሕዝቦች ማንነት፣ ባህል፣ ቋንቋና ታሪክ ከማስተዋወቅ አንፃር መልካም አፈጻጸም ነበረው።

ሆኖም የሀገርን አንድነት የሚያጠናክሩ ጉዳዮችን ያላካተቱ በመሆናቸው ክፍተቱን በመገምገም 15ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል አንድነትና ትሥሥር ይበልጥ በሚያጠናክር መልኩ ለማክበር ዝግጅት መጀመሩን ተናግረዋል።

በዓሉ ሕገመንግሥቱ ለሕዝቦች የሰጠውን እኩልነት፣ ነፃነትና አንድነት ለማሳወቅ ጭምር ነው ያሉት አፈጉባዔው፤ በዓሉ በየዓመቱ ቀኑን ጠብቆ ከመዘከር ባለፈ በሕዝቦች መካከል ያመጣውን ለውጥና ውጤት እየለካን የምንሄድበት ይሆናል ብለዋል።

በዚህም የጋራ እሴት፣ ማንነትና አንድነት ለማጠናከር የሀገሪቷ ብሔር በሔረሰቦችና ሕዝቦች ትሥሥር እውን እንዲሆን መገናኛ ብዙሃን 15ኛው በዓል በደመቀ ሁኔታ የተሳካ እንዲሆን በሙያቸው በመደገፍ የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

በዓሉ ሀገሪቱ ከነበረችበት ችግር እንድትወጣ ነባራዊ ሁኔታዎች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆን እንዳለበት የተናገሩት ደግሞ በመድረኩ የተካፈሉት የኢሳት ቴሌቪዥን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ናቸው።

የሀገር ህልውናን ለማስቀጠል ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በመገንባት የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነት እውን ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የዋልታ ቴሌቪዥን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ታሪኩ ለገሠ በበኩላቸው በዓሉ ሀገራዊ አንድነትን ማስቀጠል የሚችል የጋራ እሴት የሚገነባበት መሆን እንደሚገባው ተናግረዋል።

15ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል የሚከበረው በድሬዳዋ አስተዳደር እንደሆነ ቀደም ሲል ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም