በአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት በጥናት ላይ ተመስርቶ እየተሰራ ነው

113

ባህርዳር፣ ነሐሴ 19/2012 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የሚነሱ ችግሮችን ለይቶ ለመፍታት በጥናት ላይ ተመስርቶ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ገለጹ።

በክልሉ ፍርድ ቤቶች ከዳኞች ተግባራት ጋር  የተያያዙ ችግሮች ላይ ተወያይቶ መፍትሄ ለመስጠት የተዘጋጀ ጉባኤ በባህርዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት አብዬ ካሳሁን በጉባኤው መክፈቻ ስነስርዓት እንደተናገሩት ለውጡ ለሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መረጋገጥ ትኩረት ሰጥቷል።

መሰረታዊ መብቶችና ነጻነቶች በህገ መንግሰትና ሌሎች ህጎች ቢደነገጉም በተሟላ ሁኔታ ለማስከበር ጠንካራ ፍርድ ቤቶችን በየደረጃው መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።

ፍርድ ቤቶችን ማጠናከር የወንጀልና ፍትሃ ብሄር ጉዳዮችን በተቀላጠፈ ሁኔታ ውሳኔ በመስጠት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።

ለዚህም በፍርድ ቤቶች የሚነሱ ችግሮችን በመለየት፣ በማጥናትና በመመርመር ለመፍታት በጥናት ላይ ተመስርቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ፍርድ ቤቶች በራሳቸው ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ባሻገር የጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉባኤ በችግሮች ላይ በመምከር የሚፈታበት አቅጣጫ ማስቀመጥ ይጠበቅበታል ብለዋል።

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ ጸጋዬ ወርቃየሁ ባቀረቡት ጽሁፍ ፍርድ ቤቶች ነጻና ገለልተኛ ሆነው የሚሰሩበት ምቹ ሁኔታ መፍጠር ህዝባዊ አገልግሎትን ለማቀላጠፍ እንደሚበጅ ገልጸዋል።

በዚህም በክልሉ ምክር ቤት በየዓመቱ ለፍርድ ቤቶች የሚመደበው በጀት አነስተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተቋቋሙለትን ዓላማና ግብ ለማሳካት ችግር እንደሚሆንባቸው ጠቅሰዋል።

በክልሉ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት እስከ ወረዳ ያሉ ዳኞች ደመወዝም ዝቅተኛ በመሆኑ ሙሉ ጊዜያቸውን ለስራቸው ብቻ እንዲሰጡ አላደረጋቸውም ብለዋል።

በሙያቸውና ስነ ምግባራቸው የተመሰገኑ ዳኞች በየጊዜው እንዲፈልሱ በማድረግ ቀልጣፋና ፍትሃዊ የሆነ የህዝብ አገልግሎት ለመስጠት አስቸጋሪ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል።

ችግሩን ለማቃለል በዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ተጠንቶ የቀረበውን የደመወዝና ጥቅማ ጥቅም መጠን የክልሉ ምክር ቤት ያለበቂ ምክንያት ቀንሶ መወሰኑ ተገቢነት የሌለው በመሆኑ እንደገና መታየት እንዳለበት አመልክተዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት የህግና ፍትህ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አማረ ሰጤ በበኩላቸው በፍርድ በቶች የሚነሱ የበጀትና ደመወዝ ጥያቄዎች በክልሉ የገቢ አቅም ላይ የሚመሰረቱ ናቸው ብለዋል።

ለክልሉ  ፍርድ ቤቶች በተጠናቀው የበጀት ዓመት 980 ሚሊዮን ብር የነበረው አጠቃላይ በጀት በተያዘው የስራ ዘመን ወደ አንድ ቢሊዮን 240 ሚሊዮን ከፍ ማለቱን አስረድተዋል።

ይህም ሆኖ ከዳኞች ደመወዝና ጥቅማጥቅም ጋር ተያይዞ የተጠየቀውን ማሻሻያ ከክልሉ ውስጣዊ አቅም ጋር በማያያዝ ምላሽ ቢሰጥም በዳኞች ላይ እርካታ አለመፍጠሩን ገልጸዋል።

ይህም የክልሉን ገቢ የመሰብሰብ አቅም በማሳደግ በቀጣይ የሌሎች ክልሎች ልምድና የክልሉን አቅም መሰረት በማድረግ እየታየ ሊሄድ የሚችል ጉዳይ ነው ብለዋል።

ጉባኤው የጀትና ደመወዝ ብቻ ሳይሆን በፍርድ ቤቶች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ላይ በመወያየት ለመፍታት ጭምር ሊሆን እንደሚገባም አመልክተዋል።

በጉባኤው የክልልና የዞን ፍርድ ቤቶች፣ የአማራ ምሁራን መማክርት ጉባኤ፣ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ፣ የምክር ቤትና  ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ናቸው።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም