የአፍሪካ የቢዝነስ ተቋማት ወደ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ሽግግር እያደረጉ ነው…ጥናት

5478

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19/2012 (ኢዜአ) የአፍሪካ የቢዝነስ ተቋማት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ሥራቸውን ለማከናወን ወደ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ሽግግር እያደረጉ መሆኑን አንድ ጥናት አመለከተ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽንና ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ አማካሪ ተቋም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአፍሪካ ኢኮኖሚ ላይ ያደረሰውን ተፅዕኖ አስመልክቶ ያደረጉትን ሁለተኛ ዙር የዳሰሳ ጥናት ግኝት ትናንት ይፋ አድርገዋል።

በበይነ መረብ አማካኝነት የተካሄደው የዳሰሳ ጥናት ከሰኔ 9 እስከ ሐምሌ 13 ቀን 2012 ዓ.ም የተካሄደ ሲሆን የአፍሪካ የቢዝነስ ተቋማት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የገጠሟቸውን ፈተናዎችና ምላሽ ያካተተ መሆኑን የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በዳሰሳ ጥናቱ ውጤት መሠረት የአፍሪካ የቢዝነስ ተቋማት አዳዲስ ደንበኞችን የማግኘት ዕድል መቀነስ፣ የፍላጎት መቀነስና የገንዘብ ፍሰት እጥረት የገጠሟቸው ዋነኛ ፈተናዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአቅርቦትና ገበያው ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል እንደፈጠረባቸውና ፍትሐዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪን እንደ ትልቅ ፈተና እንዳዩትም አመልክተዋል።

በዳሰሳ ጥናቱ ከተሳተፉ ኩባንያዎች ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ መንግሥት ባደረገላቸው ድጋፍ ያን ያህል እርካታ እንዳልተሰማቸው መግለጻቸውን የዳሰሳ ጥናቱ አሳይቷል።

25 በመቶ የሚሆኑ ኩባንያዎች ድጋፍ ከጠየቁባቸው የፋይናንስ ተቋማት መልካም ምላሽ እንዳገኙና 42 በመቶው በፋይናንስ ተቋማቱ ከፍተኛ ወለድ መጠን መጠየቅ፣ የአገልግሎት መዘግየትና የብድር ማስያዣ (ኮላተራል) ቅድመ ሁኔታዎች ደስተኛ እንዳልሆኑም በጥናቱ ተመልክቷል።

በዳሰሳ ጥናቱ የተካተቱት ኩባንያዎች በግማሽ አቅማቸው እየሰሩ እንደሚገኙና እ.አ.አ በ2020 ገቢያቸው በ18 በመቶ ሊቀንስ እንደሚችል ተጠቅሷል።

በቀጣይ ሦስት ወራት ኩባንያዎቹ 20 በመቶ የሚሆኑ ሠራተኞቻችውን ይቀንሳሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን 27 በመቶ የሚሆኑ ሠራተኞች በቤታቸው ሆነው እንዲሰሩ መደረጉ የተቀናሾቹን ቁጥር ከዚህ ሊጨምረው ይችል ነበር ተብሏል።

በዕቃ ሽያጭ ላይ የተሰማሩ የአነስተኛ ዝቅተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲሁም በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ትላልቅ ኩባንያዎች ቤት ውስጥ ሆኖ መሥራት ፈተና እንደሆነባቸው ገልጸዋል።

በኩባንያዎቹ ሴቶች ከወንዶች በበለጠ ከሥራ የመቀነስ ዕድላቸው ሰፊ እንደሆነና ይህ የሆነበት ምክንያት ሴቶች ይበልጥ በአነስተኛ፣ ዝቅተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ተቀጥረው የመሥራት ዕድላቸው ሰፊ ነው በሚል በጥናቱ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው ኩባንያዎች ገልጸዋል።

ሁለት ሦስተኛዎቹ የዳሰሳ ጥናቱ ተሳታፊዎች ኮቪድ-19 ባስከተለው ቀውስ ሥራቸውን ማስቀጠል የሚችሉባቸው አዳዲስ ዕድሎች ማግኘታቸውን መግለጻቸው እንደ መልካም ግኝት ተወስዷል።

የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ቀጣናዊ ትሥሥርና የንግድ ሥራ ክፍል የኢኮኖሚ ጉዳዮች ኦፊሰር ሲሞን ሜቬል በዳሰሳ ጥናቱ ኮቪድ-19 ያስከተለውን ቀውስ ተከትሎ አዳዲስ አማራጮችን ወደ መጠቀም መግባታቸውን ገልጸዋል።

በተለይም በዕቃዎች ሽያጭ ላይ በተሰማሩ አነስተኛ ዝቅተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚሰሩ ሴቶች አዳዲስ ዕድሎችን የመጠቀም አቅማቸው የተሻለ እንደሆነ በጥናቱ ለማወቅ ተችሏል ብለዋል።

የአፍሪካ የቢዝነስ ተቋማት አዳዲስ ዕድሎችን መጠቀም መጀመራቸው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ወደ መጠቀም እየተሸጋገሩ እንደሆነ ማረጋገጫ እየሆነ ነው ሲል የዳሰሳ ጥናቱ ሪፖርት አመልክቷል።

ተቋማቱ በበይነ መረብ የታገዙ የግብይት አማራጮች በተለይም የኤሌክትሮኒክስ ንግድ (ኢ-ኮሜርስ) በማበልጸግ እየተጠቀሙ መሆኑም ተገልጿል።

በኢንተርኔት ተደራሽነት ችግር፣ በክፍያ አማራጮች፣ በሎጂስቲክስና ትራንስፖርት አቅርቦት ምክንያት በአፍሪካ ከኤሌክትሮኒክስ ንግድ (ኢ-ኮሜርስ) የሚገኘው የገቢ ድርሻ 16 በመቶ እንደሆነና ይህም ትንሽ የሚባል እንደሆነም ጥናቱ አመላክቷል።

በዳሰሳ ጥናቱ ከተካተቱት ኩባንያዎች 47 በመቶ የሚሆኑት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ላመጣባቸው ችግር መፍትሔ ለማግኘት በአጋርነትና በትብብር በፈጠሯቸው ማዕቀፎች የፈጠራና የዲጂታል አማራጮች ሽግግር እያደረጉ ወይም ለማድረግ ዕቅድ እንዳላቸው መግለጻቸውን የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን መግለጫ ያሳያል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን እ.አ.አ በ2020 በ3 ነጥብ 2 በመቶ ያድጋል ተብሎ የተተነበየው የአፍሪካ የኢኮኖሚ ዕድገት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ወደ 1 ነጥብ 8 በመቶ ዝቅ እንደሚል በግንቦት 2012 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ወረርሽኙ በአፍሪካ የንግድ ተቋማት በተለይም በጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለ ኢንተርፕራይዞች ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጫና ማሳደሩን ይህም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሥራአጥ ማድረጉንም ገልጾ ነበር።