በነሐሴ አጋማሽ ቀናት ከ256 ሺህ በላይ ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ተደረገላቸው

39

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 19/2012(ኢዜአ) ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በተያዘው ወር እየተካሄደ ባለው የማኅበረሰብ ንቅናቄና የምርመራ ዘመቻ በ15 ቀናት ከ256 ሺህ በላይ ሰዎች ምርመራ እንደተደረገላቸው የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በሰጡት መግለጫ በዚህ ወር የተጀመረው የማኅበረሰብ ንቅናቄና የምርመራ ዘመቻ በሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።

በዘመቻው የአፍና አፍንጫ መሸፈን መርሃ ግብር /ማስክ ኢትዮጵያ/ መጠናከሩን ገልጸው ክልሎችም መርሃ ግብሩን በራሳቸው መንገድ እየሰሩበት መሆኑን ጠቁመዋል።

ለአብነትም ሀረሪ፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ሲዳማና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ግንባር ቀደም መሆናቸውን ጠቁመው ሌሎችም ተመሳሳይ ሂደት ላይ ናቸው ብለዋል።

ዘመቻው በተለያዩ የመገናኛ ስልቶች እንዲሁም ቤት ለቤት በመሄድ በማስተዋወቅ ኅብረተሰቡ በዘመቻው ተሳታፊ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ጎን ለጎንም በተለይ ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ የሥራ ክፍሎችና ግለሰቦችን በመለየት ሠፊ የምርመራ ሥራ በዘመቻው መሠራቱን አስረድተዋል።

በዚህም በመጀሪያዎቹ የነሐሴ 15 ቀናት ብቻ ከ256 ሺህ በላይ ዜጎች መመርመራቸውንና ይህም ከዕቅዱ በላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቀሪ የወሩ ቀናት 270 ሺህ ሰዎችን ለመመርመር መታቀዱን ነው ዶክተር ሊያ የገለጹት።

ዘመቻው ከመጀመሩ በፊት 65 በመቶ የሚሆነው ምርመራ በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ባሉ አከባቢዎች እንደነበር ገልጸው በዘመቻው የአዲስ አበባና ዙሪያዋ ድርሻ 28 በመቶ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀሪው 72 በመቶ የዘመቻ ምርመራ የቫይረሱን ስርጭትና ያለበትን አገራዊ ሁኔታ ለመረዳት በሌሎች የአገሪቷ ክፍሎች ትኩረት መደረጉን ጠቁመዋል።

በተጓዳኝ ኅብረተሰቡ ወቅቱ የወረርሽኝ መሆኑን በመረዳት የሚያደርጋቸውን የጥንቃቄ እርምጃዎች ይበልጥ ሊያጠናክር እንጂ ሊዘናጋ አይገባም ብለዋል።

ያም ሆኖ አሁን አሁን በቤተ-እምነቶችና በተለያዩ ሥፍራዎች በብዛት መሰብሰብ እንዳለና አካላዊ ርቅትን መጠበቅ ላይም መዘናጋት መኖሩን ጠቁመዋል።

ይህ መዘናጋት ዋጋ እንዳያስከፍል መጠንቀቅ ይገባል ያሉት ሚኒስትሯ በተለይ ወረርሽኙ ይበልጥ እንዲስፋፋ የሚያደርጉ ሁኔታዎችን መቀነስ ይገባል ብለዋል።

ኅብረተሰቡ ለመጪዎቹ የበዓላት ሰሞን ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲያደርግም ሚኒስትሯ አሳስበዋል።

በቫይረሱ ሕይወታቸውን እያጡ ያሉ ሰዎች ሌሎች ተጓዳኝ በሽታዎች የሌሉባቸው መሆናቸውን በመገንዘብ ጥንቃቄው ሊጠናከር ይገባልም ብለዋል።

ወረርሽኙን ከመከላከል ጎን ለጎን ሌሎች መደበኛ የጤና አግልግሎቶች ሳይስተጓጎሉ ተጠናክረው መቀጠላቸውንም ዶክተር ሊያ ገልጸዋል።

የጤና ባለሙያዎች አገልግሎታቸውን በጥንቃቄ ለማኅበረሰቡ ማቅረብ፤ ኅብረተሰቡም ያለ ስጋት አገልግሎቶቹን ማግኘት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

እስከ ትናንት ባለው መረጃ በኢትዮጵያ ከ775 ሺህ በላይ ሰዎች ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን ከእነዚህ መካከል ከ42 ሺህ በላይ ዜጎች በቫይረሱ እንደተያዙ ተረጋግጧል።

15 ሺህ 262 ሰዎች ከቫይረሱ ማገገማቸውን፤ 692 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉንም የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም