በምዕራብ ጉጂ ዞን ለመንግስት ሰራተኞች 16 ሺህ 200 ካሬ ሜትር የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ተሰጠ

36

ነገሌ፣ ነሐሴ 19/2012 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ቶሬ ከተማ አስተዳደር ለመንግስት ሰራተኞች ከሊዝ ነጻ የሆነ 16 ሺህ 200 ካሬ ሜትር የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ሰጠ፡፡

የከተማው አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገመቹ ቡጡ የመንግስት ሰራተኛውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ለሁለተኛ ዙር የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ከተረከቡ 81 የመንግስት ሰራተኞች መካከል 6 ሴቶች እና 2 አካል ጉዳተኞች እንደሚገኙበት ተናግረዋል፡፡

ከሰራተኞቹ ለዓመታት ሲነሳ የነበረው የመኖሪያ ቤት ችግር በመልካም አስተዳደር ጉድለት ምላሽ ሳያገኝ እስካሁን መቆየቱንም አስታውሰዋል፡፡

በመጀመሪያ ዙር ለ73 ሰራተኞች አሁን ደግሞ ለ81 ሰራተኞች በአጠቃላይ 30 ሺህ 800 ካሬ ሜትር ቦታ መሰጠቱን አስታውቀዋል፡፡

የቶሬ ከተማ አስተዳደር ከመንግስት ሰራተኛው የሚነሳውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል የሚደረገው ጥረት እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል፡፡

የከተማውን እድገትና ልማት በማፋጠንና ለነዋሪዎቹ ምቹ፣ ጽዱና ውብ ለማድረግ 2 ሚሊዮን ብር ተመድቦ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

የወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ሰራተኛና የአካል ጉዳተኛ ወጣት ጉዮ ገመዴ በየወሩ የሚከፍለው የኪራይ ገንዘብ በፈጠረበት የኑሮ ጫና  የመንግስት ስራውን ተረጋግቶ እንዳይሰራ እንቅፋት ሆኖበት መቆየቱን ተናግሯል።

ችግሩን ለማቃለል በተሰጠው ቦታ የመኖሪያ ቤት ለመስራት ጥረት እንደሚያደርግ አመልክቷል።

ሌለው  የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኛ አቶ ዮሐንስ አጋ በበኩላቸው ቤት ለመስራት ሲያቀርብ የነበረው ዓመታት ጥያቄው ምላሽ በማግኘቱ ቤተሰቦቹንና ጓደኞቹን አስተባብሮ በአጭር ጊዜ የመኖሪያ ቤት ሰርቶ ችግሩን ለማቃለል እንደሚጥር  ገልጸዋል፡፡

ይህም የመኖሪያ ቤት ችግራቸውን በመፍታት በተሰማሩበት መስክ የተሻለ ለመፈጸም  የሚያተጋቸው መሆኑን ሰራተኞቹ ገልጸዋል።