ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ ለሆኑ ሴቶችና ሕፃናት የሚደረገው ድጋፍ መጠናከር አለበት

60

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 19/2012(ኢዜአ) ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ ከሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተለይ ለሴቶችና ሕጻናት የሚደረገው ድጋፍ ሊጠናከር ይገባል ተባለ።

ሆፕ ኦፍ ጀስቲስ የሴቶችና ሕጻናት ማቆያ 700 ሺህ ብር ግምት ያላቸው የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉ በአዲስ አበባ ለሚገኙና ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ ለሆኑ ቤተሰቦች፣ የፖሊስ አባላት እንዲሁም በከተማ አስተዳደሩ ሴቶችና ሕጸናት ቢሮ ስር ለሚገኙ የሕጻናት ማቆያ ተቋማት ነው የተበረከተው።


ግብረ ሰናይ ድርጅቱ የቁሳቁስ ድጋፉን ሲያስረክብ የተገኙት የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አለሚቱ ኡሙት ለቫይረሱ ተጋላጭ ከሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተለይ ለሴቶችና ሕጻናት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

የቫይረሱን ስርጭት በአጭር ጊዜ መግታት እንዲቻል ሁሉም ሰው በጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮችን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የሆፕ ኦፍ ጀስቲስ የሴቶችና ሕጻናት ማቆያ የፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ደረጄ ዘለቀም ቫይረሱን የመከላከሉ ተግባር የሁሉንም ርብርብ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

በዚሁ መሰረት ድርጅቱ እያንዳንዳቸው 20 ሺህ ሊትር የሚይዙ ሶስት የውሃ ማጠራቀሚያዎች እንዲሁም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል፣ ሳኒታይዘርና ሳሙና ማበርከቱን ገልጸዋል።


ድጋፍ ከተደረገላቸው ተቋማት መካከል የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን የወከሉት የኮሚሽኑ የሴቶችና ሕጻናት ዘርፍ ዳይሬክተር ኮማንደር አፀደ ሆርዶፋ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

የኮሮናን ቫይረስ ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ኅብረተሰቡ ከመዘናጋት በመቆጠብ ራሱንና ወገኑን መጠበቅ እንዳለበትም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም