በህገ-ወጥ መንገድ የተያዙ የወል መሬትን በማስመለስ ወጣቶችና ሴቶች እንዲጠቀሙበት ይደረጋል- አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

127
ባህርዳር ሀምሌ 5/2010 በህገ-ወጥ መንገድ የተያዘውን የወል መሬት በማስመለስ ወጣቶችና ሴቶች እንዲጠቀሙባቸው በማድረግ በኩል በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተናገሩ። ርዕሰ መስተዳደሩ የክልሉን የ 2010 ዓ.ም በጀት ዓመት የ11 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል። በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በግለሰቦች ተይዞ የነበረውን የወል መሬት የማስመለስ ስራ እየተከናወነ ቢሆንም አሁንም ሰፊ  የወል መሬት በግለሰቦች እጅ ተይዘው ይገኛሉ። በበጀት ዓመቱ በግለሰቦች ተይዞ የነበረ 13 ሺህ ሄክታር የገጠር መሬት እንዲመለስ መደረጉን ገልፀው ከዚህም ውስጥ 8 ሺህ 500 ሄክታሩ ለወጣቶች፣ ሴቶችና ወላጆቻቸውን ላጡ ህጻናት ተሰጥቷል። ወጣቱ ሰርቶ ለመለወጥ መሬት መሰረታዊ ጥያቄው ሆኖ እያለ በህገ-ወጥ መንገድ የወል መሬት ለግላቸው ጥቅም የሚያውሉ ግለሰቦችን መለየትና መሬቱን አስመልሶ ለሚገባው አካል መስጠት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ የክልሉ መንግስት የመልካም አስተዳደር ችግርን ይፈታል ተብሎ የታመነበት በካርታ የተደገፈ የሁለተኛ ደረጃ  የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር በመስጠት ላይ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡ ይህንን ተግባር ለማፋጠን ይረዳ ዘንድ 17 ሺህ 165 ካሬ ኪሎ ሜትር የአየር ፎቶ እንዲነሳ ተደርጓል። ይሁን እንጂ ክልሉ ሙሉ ለሙሉ በአየር ፎቶ እንዲሸፈን ቢደረግም የሁለተኛ ደረጃ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተርን በማዳረስ በኩል በታሰበው ልክ እየተከናወነ አይደለም። ለዚህ ደግሞ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችና አመራሮች በተደራጀና እውነታን መሰረት ባደረገ መረጃ ተንተርሰው መስራት አለመቻላቸው ነው። ርዕሰ መስተዳደሩ እንደገለጹት የመሬት መልካም አስተዳደር ችግርን የሚቀርፈው የሁለተኛ ደረጃ ደብተርን ለማዳረስ እየተሰራ ባለበት በአሁኑ ወቅት አሁንም የመጀመሪያ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ የሚሰጠበት ሁኔታ አለ። ይህ ደግሞ በዘርፉ ላይ የተሰማራው ባለሙያና አመራር የሚሰራውን ስራ ጠንቅቆ ካለማወቅ የመነጨ ሲሉም አብራርተዋል። ይህም በዘርፉ የሚሰሩ ባለሙያዎችና አመራሮች በተጨባጭ መረጃ ላይ ሳይመሰረቱና  በግምት እየሰሩ መሆናቸውን አመላካች መሆኑን ገልፀው በቀጣይ ከእንደዚህ አይነት በመረጃ ያልተደገፈ አሰራር መውጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል። ርዕሰ መስተዳደሩ አክለውም የክልሉ ብዙሃን መገኛናና በየደረጃው ያሉ የመንግሰት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤቶች የክልሉን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ህብረተሰቡ በንቃት እንዲሳተፍ እየሰሩ ቢሆንም አሁንም ሰፊ ስራ እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል። በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ  ህብረተሰቡ  በቂ መረጃ እንዲኖረውና ለልማትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ  የድርሻውን እንዲወጣ  የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡ በዋና ዋና አገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት እንዲኖር ሚዛናዊ መረጃዎችን  በማጠናቀር ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ ወቅቱ የሚፈልገው ጉዳይ ነው። “ህብረተሰቡ ከመቸውም  ጊዜ በላይ ወቅታዊ መረጃዎችን የሚፈልግ መሆኑን በመገንዘብ ይህንን በሚመጥን ደረጃ መስራት ያስፈልጋል'' ነው ያሉት። ለመልካም አስተዳደር ስራ ህብረተሰቡን ማነቃቃትና  የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትንና አንድነት የማጠናከር  ስራ  በበለጠ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። ዘርፉ በመረጃ የበለጸገና ምክንያታዊ ህብረተሰብ ለመፍጠር  የሚያስችል እንደመሆኑ  የላቀ ስራ መስራት እንደሚጠበቅበትም ተናግረዋል፡፡ ትናንት የተጀመረው የክልሉ ምክር ቤት 10 ኛ መደበኛ ጉባኤ ለአራት ቀናት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በመምከር የተለያዩ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።                          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም