የሚኒስቴሩ የአመራር አባላት የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለገበታ ሀገር ፕሮጀክት ትግበራ እንዲውል ወሰኑ

57

አዲስ አበባ፣ነሐሴ 17/2013 (ኢዜአ) የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር የአመራር አባላት የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ትግበራ እንዲውል ወሰኑ።

የአመራር አባላቱ የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ትግበራ እንዲውል መወሰናቸውን  ሚኒስቴሩ ዛሬ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ፕሮጀክቱ ለሴቶችና ወጣቶች ተሳትፎና የሥራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት በመስጠቱ ሚኒስቴሩ ኢኮኖሚውን ይደግፋል የሚል ተስፋ እንዳለውም ነው ሚኒስቴሩ በመግለጫው ያመለከተው።

ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ስኬታማ እንዲሆን በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ያሉ የዘርፉ አደረጃጀቶች፣ ሲቪክ ማህበራት፣ ሴቶችና ወጣቶች የቻሉትን ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ ቀርቧል።

ሚኒስቴሩ የሴቶችና ወጣቶችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እንዲሁም የህጻናትን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ ከለውጥ አመራሩ ጋር እየሰራ ይገኛል።

ከዚህ በተጨማሪ እንደ አገር የገጠሙ ወቅታዊ ችግሮችን ከአጋር አካላት ጋር በመወያየትና በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖች ያሉበትን ሁኔታ ተረድተው ድጋፍ እንዲያደርጉ በማድረግ በኩል ውጤታማ ሥራ እየተሰራ መሆኑን በመግለጫው ተገልጿል።

በ2013 ወደ ትግበራ የሚገባው የሚኒስቴሩ የአሥር ዓመት ዕቅድ የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶችን አንኳር ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ለሚያስችል አሰራር ትኩረት ሰጥቷል።

ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶች ለአገር ከሚኖራቸው ጠቀሜታ ባሻገር ህዝቦችን እርስ በርስ በማስተሳስር ብሔራዊ መግባባትን እና የይቻላል መንፈስን ለመፍጠረ የሚያስችሉ ሚኒስቴሩ በመግለጫው አመልክቷል።

የልማት ፕሮጀክቶቹ ለኢትዮጵያ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች የብልጽግና ተስፋን ከማጎናጸፍ ባለፈ የአመራሩን ሞራል የሚገነቡና ለላቀ ሃሳብ የሚያነሳሱ መሆናቸውንም አስታውቋል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም