እንጦጦና ሸገር ፓርኮች የቱሪስት ቆይታ ጊዜ እንዲጨምር ዕድል ይፈጥራሉ - በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች

104

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቱር ኦፕሬተሮች እንጦጦና ሸገር ፓርኮችን ጨምሮ በአዲስ አበባ እየተገነቡ ያሉ የመዝናኛ ሥፍራዎች የቱሪስት ቆይታ እንዲጨምር ዕድል የሚፈጥሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በቱሪዝም ኢትዮጵያና የቱር ኦፕሬተሮች ማኅበር አማካኝነት በቱሪዝም ዙሪያ የሚሰሩ ድርጅቶች እንጦጦና ሸገር ፓርኮችን ጎብኝተዋል።

አቶ ያሬድ ሙሉጌታ ፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ አገሮች ላይ መሠረት አድርገው ቱሪስቶች ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ በማመቻቸትና በማስጎብኘት ሥራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ።

'ሞንፔይስ ቱርስ' ዋና ኃላፊው አቶ ያሬድ ቱሪስቶች ሌሎች አገሮችን ጎብኝተው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ለማቆየት ከባድ እንደነበር ያስታውሳሉ።

''አሁን ግን በቅርቡ ወደ ሥራ ሊገቡ ዝግጅት ላይ ያሉት የእንጦጦ ፓርክና የሸገር ወይም የወዳጅነት ፓርክ ትልቅ ዕድል ይፋጥራሉ'' ብለዋል።

በትንሹ አንድን ቱሪስት ካሰበው በተጨማሪ አንድ ምሽት በአዲስ አበባ እንዲያሳልፍ ሊያደርጉ የሚችሉ ናቸው።

በተጨማሪም የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪዎቹ ተፈጥሮ አድናቂና በጫካ ውስጥ የእግር ጉዞ ማድረግ ስለሚወዱ እንጦጦ ተማራጭ እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል።

'የባላገሩ አስጎብኚ' ሥራአስኪያጅ አቶ ተሾመ አየለ በበኩላቸው ኢትዮጵያን ለመሸጥ ትልቅ አቅም የሚሆኑ መዳረሻዎች መጨመራቸውን ተናግረዋል።

''ከዚህ በፊት ቱሪስት በአዲስ አበባ አንድ ቀን የሚቆይ ከሆነ ከዚህ በኋላ ሦስትና አራት ቀን መቆየት እንዲችል ያደርገዋል'' ብለዋል።

ይህ ደግሞ ለአስጎብኚዎችም ለአገሪቷም ትልቅ ጥቅም መሆኑን ተናግረው፤ በቀጣይ እንደዚህ ዓይነት ፕሮጀክቶች እንዲሰፉ ጠይቀዋል።

ሌላው 'ኢትዮጵያ ትራዲሽናል ቱርስ' አስጎብኚው ወጣት ዮሐንስ ተክሌ ''ሸገርን ማስዋብ ትልቅ ጥቅም ያለው ነው'' በማለት ገልጾ፤ ይህም የቱሪዝም ዘርፉን የሚያበረታታ መሆኑን ተናግሯል።

የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ሥራአስፈጻሚ አቶ ስለሺ ግርማ ''ፕሮጀክቶቹ በመጠናቀቃቸው አሁን የማስተዋወቂያ ጊዜ ነው'' ብለዋል።

ከዚህ በፊት ዕቅድ የሚያዘው አዲስ አበባ ውስጥ የቱሪስት ቆይታ አንድ ወይም ሁለት ቀን እንደነበረ አስታውሰው፤ በፕሮጀክቶቹ መጠናቀቅ የቱሪስቶች የቆይታ ጊዜ እንደሚሻሻል ገልጸዋል።

አቶ ስለሺ አክለውም ''በተለይ ፕሮጀክቶቹ የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ለስሟ የሚመጥኑ የመዝናኛ ሥፍራዎች ናቸው'' ብለዋል።

ፕሮጀክቶቹ ቱሪዝምን ከማበረታታት በተጨማሪ ለገጽታ ግንባታም ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለቸው ገልጸዋል።

ፕሮጀክቶቹን የጎበኙት የዘርፉ ተዋናዮች እነዚህን ፕሮጀክቶች አቅደው ወደ ተግባር ለቀየሩት አካላት ትልቅ ምሥጋና እንዳላቸውም ገልጸዋል።

250 አባላት ያሉት የኢትዮጵያ ቱር ኦፕሬተርስ ማኅበር አባላት ከጉብኝቱ በኋላ በእንጦጦ ፓርክ ችግኝ ተክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም