ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀዝቃዛ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ጀመረች

አዲስ አበባ ነሀሴ 16/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀዝቃዛ

የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን በባቡርና በመርከብ አቀናጅታ ለውጭ

ገበያ ማቅረብ ጀመረች። 

አቮካዶ የጫነ የመጀመሪያው ኮንቴነር ዛሬ ከሞጆ ደረቅ ወደብ ወደ አውሮፓ ለሙከራ ተልኳል።

የትራንስፖርት ሚኒስቴሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ምርቶቹ ለውጭ ገበያ መቅረባቸው በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ አርሶ አደሮችና ወጣቶች ምርቶቻቸውን ለዓለም አቀፍ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ አንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።

እንዲሁም ለውጭ ምንዛሪ ግኝት ዕድል በመፍጠር ረገድም  ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

በቀጣይም አርሶ አደሩ የግብርና ምርቶቹን ጥራታቸውን እንደጠበቁና ሳይበላሹ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ለማድረግ እንተጋለን ብለዋል።

ለዚህም የባቡርና መርከብ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን ምርቱ በሚመረትበት ሥፍራ በትኩስነቱ እንዲመጣ የማቀዝቀዣአገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች እንደሚቀርቡ ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

በዚህም ቀጣይነት ያለው የምርት አቅርቦት እንዲኖር በማድረግ የዜጎችን ተጠቃሚነትና የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ ይሰራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም