ሕንድ የተለያዩ መድኃኒቶችን ለኢትዮጵያ ድጋፍ አደረገች

ነሃሴ 15/2012(ኢዜአ) ሕንድ የተለያዩ መድኃኒቶችን ለኢትዮጵያ ድጋፍ አደረገች።

ድጋፉን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በኢትዮጵያ የሕንድ ኢምባሲው ቅጥር ግቢ ተገኝተው ተቀብለዋል።

በኤምባሲው በኩል ዛሬ የተደረገው ድጋፍ 100 ሺህ የሚወሰዱ ኪኒኖችና ኮሮናቫይረስን ለመቋቋም የሚረዱ አንቲባዮቲክ መድኃኖቶች ናቸው።  

በኢትዮጵያ የሕንድ ምክትል አምባሳደር ሞሃን ላል በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ ኢትዮጵያና ሕንድ በጤናው ዘርፍ በበርካታ ጉዳዮች ላይ በትብብር እየሰሩ ይገኛሉ።

መድኃኒቶችን ድጋፍ በማድረግ እና የጤና ባለሙያዎችን በማሰልጠን በጋራ እየሰሩ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል አምባሳደሩ፣ 3 ሺህ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ወደ ሕንድ ሄደው እንዲታከሙ ቪዛ መሰጠቱንም አመልክተዋል።    

በተለይ ኢትዮጵያና ሕንድ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በጋራ ለመከላለል ቁርጠኛ መሆናቸውን የሁለቱ አገራት መሪዎች ባደረጉት ውይይት ማረጋጣቸውንም አስታውሰዋል።  

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ እየተስፋፋ መሆኑን ጠቁመው፣ ድጋፉ ወረርሽኙን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ኢትዮጵያና ሕንድ በህክምና ቱሪዝም የረጅም ጊዜ ግንኙነት እንዳላቸው ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታው "በሕክምና ቁሳቁስም ትልቅ አጋራነት አላቸው" ብለዋል።

ለዚህም የሕንድ መንግስት ቀደም ሲል ድጋፍ ያደረገው "ሲቲ ስካን መመርመሪያ መሳሪያ" በየጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ትልቅ ግልጋሎት እየሰጠ መሆኑን አመልክተዋል።

በመድኃኒት ግዥ ላይም ኢትዮጵያ ጥራት ያለው መድኃኒቶችን ከሕንድ እያገኘች መሆኑን ጠቅሰው፣ ከሕንድ ጋር በመተባበር በአጭርና ረጅም ጊዜ ስልጠና የባለሙያዎችን አቅም የማሳደግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

"ዛሬ የተገኘው ድጋፍ ኮሮናቫይረስን በመከላከል በኩል አስተዋጽኦው የጎላ ነው" ብለዋል።

ዶክተር ደረጀ ሕንድ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥልም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ሕንድ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከጀመሩ 70 ዓመታት እንዳስቆጠሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም