ሚኒስቴሩ ተተኪ መሪዎችን በማፍራት ፕሮግራም ያሰለጠናቸውን ባለሙያዎች አስመረቀ

76

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15/2012 (ኢዜአ) የጤና ሚኒስቴር በጤናው ዘርፍ ተተኪ መሪዎችን በማፍራት ፕሮግራም ያሰለጠናቸውን ባለሙያዎች ዛሬ አስመረቀ።

በምርቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንዳሉት በጤናው ዘርፍ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት በቂ የሆነ አመራር ያስፈልጋል።

የዛሬው ምሩቃንም በጤናው ዘርፍ የተያዙ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ዕቅዶችን በአግባቡ ለመተግበር ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።

በተለይ የኮሮና ቫይረስ በተስፋፋበትና ብቁ የጤና ባለሙያና አመራር በሚያስፈልግበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የሰለጠነ ባለሙያ ማግኘት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።

ዶክተር ሊያ እንዳሉት በዘርፉ የበቃ አመራር በበቂ ሁኔታ አለመኖር በጤና ዘርፍ መሰራት ያለባቸው በርካታ ተግባራት በሚፈለገው ፍጥነት እንዳይተገበሩ አድርጓል።

ዛሬ ከተመረቁት 21 ባለሙያዎች ውስጥ 60 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸው በአመራር ቦታ ላይ ብዙ ሴቶችን ለማፍራት ለተያዘው ዕቅድ መሳካት የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል።

ምሩቃኑ በሥልጠና ወቅት ያገኙትን ዕውቀት በጥራትና በትጋት ወደ ሥራ በመተግበር ለሌሎች አርአያ እንዲሆኑም ዶክተር ሊያ አሳስበዋል።

ሥልጠናው በቀጣይ በክልል በጤና ዘርፍ ለተሰማሩና በጤና ሚኒስቴር ሥር ለሚገኙ ኤጀንሲዎች ላይ ለሚሰሩ ባለሙያዎች እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

ለምረቃ ከበቁት መካከል ወይዘሪት እህተማርያም ሻምበል ''በሥልጠና ወቅት በንድፈ ሀሳብና በተግባር ያገኘነው ዕውቀት ለተሻለ ሥራ የሚያነሳሳ ነው።'' ብላለች።

በሥልጠና ቆይታቸው ያገኙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት ጥረት እንደሚያደርጉም አመልክታለች።

ሥልጠናው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የተሰጠ ሲሆን ሠልጣኞችም ለተከታታይ ስድስት ወራት የተግባርና የንድፈ ሀሳብ ትምህርት ማግኘታቸው ተመላክቷል።

በጤናው ዘርፍ ተተኪ መሪዎችን ማፍራት ላይ ያተኮረው ይህ የሥልጠና ፕሮግራም ባለፈው ዓመት የተጀመረ ሲሆን የዛሬው ምሩቃን የመጀመሪያ ዙር ሠልጣኞች መሆናቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም