የተደረገልን የመኖሪያ ቤት ድጋፍ ከአላስፈላጊ እንግልት ገላግሎናል-ስደተኛ ሶማሌያውያን

60
አዲስ አበባ  ሀምሌ 5/2010 የተደረገላቸው የቤት ድጋፍ በየጊዜው ነፋስ ከሚያፈርሰው ደሳሳ ጎጆ እንደገለገላቸው ኢዜአ ያነጋገራቸው በዶሎ አዶ ስደተኞች ጣቢያ ውስጥ የሚኖሩ ሶማሌያውያን  ተናገሩ። አክሽን ፎር ዘ ኒዶ የተባለ አገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅት እ.አ.አ በ2018 በጣቢያው የሚኖሩ ስደተኞችን የብሎኬት ቤት ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት በይፋ ጀምሯል። ድርጅቱ ከዚህ ቀደም ዶሎ አዶ ስደተኞች ጣቢያ የብርሀሚኖራ ሃሎዌ ካምፖች ለሚኖሩ ስደተኞች 104 የብሎኬት እና 200 የቀርከሃ ቤቶችን ገንብቶ ለነዋሪዎች አስረክቧል። አሁን በይፋ ባስጀመረው የመጠለያ ግንባታ ፕሮጀክትም 438 የብሎኬት ቤቶችን ገንብቶ ለስደተኞች እንደሚያስተላልፍ ገልጿል። ኢዜአ በአካባቢው ተገኝቶ ካነጋገራቸው የቤት ተጠቃሚዎች መካከል ወይዘሮ ፋጡማ መሃመድ እንዳሉት፤ ከአካባቢው ሞቃታማ የአየር ሁኔታ ጠባይ አንጻር ተጠልለውበት የነበረው ጎጆ በተደጋጋሚ ጉዳይ ይደርስበት ነበር። ተሰርቶ የተሰጣቸው የብሎኬት ቤት ችግራቸው ተቀርፎ ተረጋግተው መኖር እንደቻሉ ተናግረዋል። ወይዘሮ ነኢማ መሃመድ በበኩላቸው ጨቅላ ልጃቸውን ይዘው አልጋ ላይ እንዳሉ ንፋስ የጎጆውን የሸራ ጣሪያ ይዞባቸው እንደሄደ አስታውሰው በተሰጣቸው ቤት ከመሳቀቅ እንዳረፉ ገልጸዋል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የስደተኞች ኮሚሽን የቀጠናው መረጃ ክፍል ባለሙያ አርያድጌ ኪፕራድ ድርጅቱ እያከናወነ ያለውን ድጋፍ አድንቀው ሌሎች ድርጅቶችም በሌሎች ሰብአዊ ድጋፎች እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል። የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ሳሊህ ሱልጣን በበኩላቸው ድርጅታቸው አቅም በፈቀደ መጠን በችግር ውስጥ ያሉ ስደተኞችን ለመርዳት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል። የሚያስገነባቸው ቤቶች ረዥም እድሜ የሚኖሩ በመሆናቸው ስደተኞች ወደ አገራቸው ሲመለሱ ለአካባቢው ማህበረሰብ የሚተላለፉ መሆኑንም አክለዋል። ድርጅታቸው ከተመድ የስደተኞች ኮሚሽን ጋር በመተባበር በአካባቢው የሰብአዊ ድጋፍ ስራን ለማፋጠን የሚያግዝ የአውሮፕላን ሜዳ ማስገንባቱንም አቶ ሳሊህ ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም