ማህበሩ ከሶስት ሺህ 600 በላይ የጎዳና ተዳዳሪዎችን የሥራ ዕድል ለማመቻቸት እየሰራ ነው

ሀዋሳ፣ ነሐሴ 14/2012 (ኢዜአ) ከሶስት ሺህ 600 በላይ ወጣቶችን ከጎዳና በማንሳት የሥራ ዕድል ለማመቻቸት ፕሮጀክት አዘጋጅቶ እየሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ ቀይመስቀል ማህበር የደቡብ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ገለጸ ፡፡
ጽህፈት ቤቱ  ለወጣቶቹ የሚሆን የጫማ ፅዳት አገልግሎት መስጫ ሼዶችንና ለኮሮና ህሙማን ማቆያ የሚውል የቁሳቁስ ድጋፍ ለዞንና ልዩ ወረዳ ቅርንጫፎች  አስረክቧል፡፡

የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ  ኃላፊ አቶ ተሾመ ታከለ  በርክክቡ ወቅት እንደተናገሩት ማህበሩ በዋንኛነት ከሚሰጣቸው የሰብዓዊ አገልግሎቶች በተጨማሪ የማህበረሰቡን መሠረታዊ ችግሮች ለመፍታት የሚያግዙ  ፕሮጀክቶችን አዘጋጅቶ እየሰራ ይገኛል።

ከእነዚህም  ጎርፍና መሰል የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን ለመከላከል የሚያስችሉ ማህበረሰብ አቀፍ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎች ይገኙበታል።

የአሁኑ ፕሮጀክትም  የዚሁ ሥራ አካል እንደሆነ ጠቅሰው፤ ይህም በተለያዩ ምክንያቶች ጎዳና የወጡ ሶስት ሺህ ሺህ 620 ወጣቶችን የሥራ ዕድል የሚያመቻች እንደሆነ  አስታውቀዋል፡፡

ለመጀመሪያ ዙር ለ10 የዞን ከተሞች ለእያንዳንዳቸው አምስት ሼዶች ተሰርቶ መታደሉንና ሥራው ቀጣይነት እንዳለውም ገልጸዋል፡፡

ማህበሩ ይህን ፕሮጀክት ዕውን ያደረገው ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እንደሆነ የተናገሩት አቶ ተሾመ ፤ ወጣቶቹ ሰርተው መለወጥ እንዲችሉ በየደረጃው ያሉ የሥራ ኃላፊዎች ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ማህበሩ  የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተስፋፋባቸው አምስት ዞኖች ለሚገኙ የውስጥ አደረጃጀት ችግር ላለባቸው ለይቶ ማቆያዎች የሚውል ሰባት ሚሊዮን ብር የሚገመት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉንም አመልክተዋል።

ቁሳቁሱ ከዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ እንደተገኘም ጠቁመዋል፡፡

የደቡብ ክልል ኢንተርፕራይዞችና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይለማርም ተስፋዬ በበኩላቸው  ፕሮጀክቱ ትኩረት ያላገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችና  ጎዳና የወጡ ወጣቶችን እንደሚጠቅም ተናግረዋል።

ወጣቶቹ የሚደግፋቸው አካል ካገኙ ሰርተው ለመለወጥ የሚያስችላቸው ጉልበትና የአእምሮ ብቃት ያላቸው እንደሆነ ገልጸው፤ ፕሮጀክቱ በሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ለምናደርገው ርብርብ ትልቅ እገዛ የሚያደርግ ነው" ብለዋል ፡፡

የክልሉ ሴቶች ፣ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አስቴር ከፍታው ሥራ አጥ ወጣት በጥፋት ኃይሎች አጀንዳ የመጠለፍ ዕድሉ ከፍተኛ በመሆኑ እነሱን ማገዝ ለችግር እንዳይጋለጡ የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክቱ የታለመለትን ግብ እንዲያሳካ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚገባና በየደረጃው ያለን የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በመደገፍ ኃላፊነታችንን መወጣት አለብን ብለዋል ፡፡

የጋሞ ዞን ቀይ መስቀል ማህበር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ስለሺ ሲሳይ በተለይ በአሁኑ ወቅት ኮሮና  ባስከተለው  ጫና   በርካታ ወጣቶች ለችግር መጋለጣቸውን አመልክተው፤ ፕሮጀክቱ የሥራ ዕድል በማመቻቸት ጫናውን ለመቀነስ እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

ፍትሀዊነትና ዘላቂ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

የሀዋሳ ከተማ ነዋሪው  ወጣት ተፉ መለሰ በሰጠው አስተያየት ከዚህ በፊት እሱና ጓደኞቹ በጎዳና በነበሩበት ወቅት በፈፀሟቸው ጥፋቶች ለእስር ተዳርገው መቆየታቸውን አስታውሷል፡፡

ከዓመታት እስር በኋላ ከማራሚያ ቤት ቢወጡም  የጎዳና ሕይወትን ለመቀጠል ተገደው እንደነበር ገልጾ ፤ ማህበሩ ለንግድ የሚሆን ሼድ በመገንባትና ሌሎች ድጋፉችን በማመቻቸት እንደታደጋቸው ተናግሯል።

በርክክቡ ስነስርዓት  የመንግስት ሥራ ኃላፊዎች፣ የዞንና የልዩ ወረዳ የማህበሩ ቅርንጫፍ ተጠሪዎችና  ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል፡፡    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም