በመጪዎቹ 10 ዓመታት በኢትዮጵያ የሚተገበረው የልማት እቅድ ውጤታማ እንዲሆን የሲቪክ ማህበራት የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
በመጪዎቹ 10 ዓመታት በኢትዮጵያ የሚተገበረው የልማት እቅድ ውጤታማ እንዲሆን የሲቪክ ማህበራት የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ ነሀሴ 14/2012(ኢዜአ) ኢትዮጵያ በመጪዎቹ 10 ዓመታት ተግባራዊ የምታደርገው የልማት ዕቅድ ውጤታማ እንዲሆን የሲቪክ ማህበራት የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ። ሲቪክ ማህበራት በበኩላቸው እቅዱ ማህበራቱ በእያንዳንዱ ዘርፍ ላይ ያላቸውን ሚና ያላመላከተ ነው ብለውታል።
ብሄራዊ ፕላንና ልማት ኮሚሽን የ10 ዓመቱን መሪ የልማት እቅድ ለሲቪክ ማህበራት ተወካዮች ገለጻ አድርጓል።
በዚሁ ጊዜ ኮሚሽነሯ ዶክተር ፍጹም አስፋው በኢትዮጵያ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ያለ ሲቪክ ማህበራቱ ተሳትፎ የሚፈለገውን ውጤት ሊያመጡ አይችሉም ብለዋል።
ማህበራቱ የዜጎችን መብትና ጥቅም ከማስጠበቅ አኳያ እያደረጉት ያለው ተሳትፎ የጎላ መሆኑን መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ፍጹም፤ በእቅዱ የመንግስትና የማህበራቱ አጋርነት የበለጠ የሚጠናከርበት አቅጣጫ መቀመጡን አመልክተዋል።
መንግስት የ10 ዓመቱን መሪ የልማት እቅድ ብቻውን ወደ ተግባር ሊቀይረው አይችልም ያሉት ኮሚሽነሯ፤ የግሉ ዘርፍ ሲቪክ ማህበራትና የልማት አጋሮች የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
'' መንግስት የራሱ ሊፈጽማቸው፣ ሊያደርጋቸው የሚችላቸው ፕሮጀክቶች እና ኢንቨስትመንቶች ቢኖሩም የግሉም ዘርፍ እንዲሁ ትልቅ ድርሻ አለው ዕቅዱ የሀገር እቅድ ስለሆነ ማለት ነው። ቀጥሎ የሲቪክ ማኅበራትና ሌሎች የልማት አጋሮችበዚሁ መጠን የራሳቸውን ድርሻ እንዲወጡና ምንድን ነው የኔ ሚና የሚለውን መለየት እነዲችሉ የዚህ ዓይነት ውይይቶች አስፈላጊ ናቸው። አሁንም እቅዱ ፋይናል እስኪሆን ድረስ የዚህ ዓይነት መድረኮች የሚቀጥሉ ይሆናል።''
በውይይት መድረኩ የተሳተፉ የሲቪክ ማህበራቱ ተወካዮች በበኩላቸው እቅዱ የዜጎችን ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት መስጠቱን አድንቀዋል።
ይሁንና ሲቪክ ማህበራት በእያንዳንዱ የልማት ዘርፍ ሊኖራቸው የሚገባውን ሚና በዝርዝር ከማስቀመጥ አኳያ ክፍተቶች ያሉበት መሆኑን ነው የጠቀሱት።
ከዚህ ባለፈ እቅዱ ተጠያቂነትን ለማስፈንና የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ግብ የሌለው መሆኑን ተችተዋል።
''በአገራችን በጣም ብዙ ጥሩ ፖሊሲዎች በጣም ጥሩ ሕጎች ወጥተዋል። እነዚህ ሕጎችና ፖሊሲዎች ተፈጻሚ ቢሆኑ አሁን በዚህ ጉዳይ ላይ የምንነጋገር አይመስለኝም። አንዱ ትልቁ ነገር ተጠያቂነት የለም፤ፖሊሲዎቹ አሉ፣ ተፈጸመ አልተፈጸመ ማን እንደሆነ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚጠየቀው አናውቅም። የሚታቀዱ እቅዶች ግልጽ የተጠያቂነት ስልቶች በአግባቡ ቢታቀዱ።''
''ከሲቪክ ማኅበራት ፕሬስፔክቲቭ የማየት እጥረት፣ሊከተሏቸው፣ ሊያግዟቸውና ሊረዷቸው የሚገቡ በርካታ ኢሺዎች አሉ። እዚያ አካባቢ የሳሳ ሆኖ ነው ያገኘሁት ዕቅዱ፤ ዕቅዱ ሙሉ እንዲሆን የሲቪክ ማኅበራት ትልቅ ጉልበት ናቸው ብሎ ከመነሳት አንጻር።''
''እቅዱ አካል ጉዳተኞች ዛሬ በሀገር ውስጥ በከፍተኛ ቁጥር እየመሩ ነው ያሉት፤ ይሄን ትልቅ ቁጥር ትቶ የበለጸገች ኢትዮጵያን ማየት በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ ዕቅዱ ድጋሚ እነዚህን ወገኖች አካቶና አወያይቶ እኛን ያማከለ ዕቅድ እንዲሆን መደረግ አለበት።አለዚያ ዕቅዱ የኔም ነው ብዮለማሰብ እቸገራለሁ።''
እንደ ዶክተር ፍጹም ገለጻ የልማት እቅዱ ረቂቅ ይፋ ከሆነ ጀምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ውይይት እያደረጉበት ይገኛሉ።
እቅዱ ከተያዘው በጀት ዓመት ጀምሮ ወደ ትግበራ እንደመግባቱ ተቋማት ከራሳቸው እቅድ ጋር አካተው ይተገብሩታል።
በእቅዱ ላይ የሚደረገው ውይይት እስከመጪው ጥቅምት ወር መጨረሻ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን እስካሁን በተካሄዱ ውይይቶች ጠቃሚ ግብዓቶች ተገኝተዋል ነው ያሉት።
''ከ18 ጊዜ በላይ-የውየይት መድረክ አድርገናል፤በነዚህ መድረኮች እውነት ለመናገር በርካታ ትላልቅ ግብዓቶች አግኝተናል። ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ትኩረት ያልተሰጣቸውና በውይይትና በልምድ በበሰሉ ሰዎች አስተያየት የተካተቱና ብዙ የሙያ ግብዓቶች እቅዱን አዳብረውታል።''