ወጣቶች የሰሩት የፈጠራ ውጤቶች ኮሮናን ለመከላከል እንዲያግዙ ተመቻችቷል

1160

መቀሌ፣ ነሓሴ 13/2012(ኢዜአ) በመቀሌ ከተማ ወጣቶች የሰሩት የፈጠራ ውጤቶች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እንዲያግዙ ለኅብረተሰቡ አገልግሎት መመቻቸታቸውን የትግራይ ክልል ሣይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ዶክተር ገብረመስቀል ገብረማርያም ለኢዜአ እንዳሉት የኮሮና ቫይረስ መከሰትን ተከትሎ ለመከላከል የሚረዱ የፈጠራ ውጤቶች በወጣቶች ሲሰሩ ቆይተዋል።

በሽታውን ለመከላከል ያግዛሉ ተብለው የተመረጡ የፈጠራ ውጤቶች ኅብረተሰቡ እንዲጠቀምባቸው ቢሮው ፍቃድና ዕውቅና መስጠቱን ተናግረዋል።

በመቀሌ ወጣት የፈጠራ ባለቤቶች ከሰሩት መካከል በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በመረጡት ቋንቋ ዕለታዊ መረጃ የሚሰጡ “ሶፍትዌር”፣ ከንኪኪ ነፃ የሆነ የእጅ መታጠቢያ፣ ለኮሮና ቫይረስ ታማሚዎች የሚያገለግል የኦክስጅን መቅዘፊያ “ቬንትሌተር” እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

እንዲሁም የፀረ ተሕዋስያን መርጫ መሣሪያዎች በመሥራት ለኅብረተሰቡ አገልግሎት እንዲውሉ መደረጋቸውን አስረድተዋል።

ወጣት የፈጠራ ባለቤቶች በሰሯቸው የፈጠራ ውጤቶች በሽታውን ለመከላከል ከማገዛቸውም በተጨማሪ ከፍተኛ የሆነ ወጪ ማዳናቸውን ዶክተር ገብረመስቀል  ገልጸዋል።

የፈጠራ ባለቤቶቹን ለማበረታታት ከንኪኪ ነፃ የሆነ የእጅ ማስታጠቢያ ለፈጠሩ ሽጠው እንዲጠቀሙ የዕውቅና ምሥክር ወረቀት እንደተሰጠ የገለጹት ዶክተር ገብረመስቀል ሶፍትዌር ለሰሩት ደግሞ በነፍስ ወከፍ 100 ሺህ ብር በሽልማት ተበርክቶላቸዋል ብለዋል።

ሳባውያን የሶፍትዌር ቴክኖሎጂ ማኅበር ሦስት አባላት የፈጠራ ዕውቀታቸውን ተጠቅመው ሶፍትዌር በማበልጸግ ሰርተው በማቅረብ ኅብረተሰቡ በቀላሉ የኮሮና መረጃ በቋንቋው እንዲያገኝ አድርገዋል።

የማኅበሩ አባል ወጣት ግርማይ አርዓያ በሰጠው አስተያየት ማኅበሩ ያበለጸገው ሶፍትዌር የኮሮና መተላለፊያ መንገዶች መረጃ ከመስጠት ባለፈ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ዕለታዊ መረጃ  በግራፍና ካርታ አስደግፎ ያቀርባል ብለዋል።

ሶፍትዌሩ ማኅበረሰቡ ራሱን ከኮሮና ቫይረስ ለመከላከል ማድረግ የሚገባቸውን ጥንቃቄ እንደሚያስተምርም ተናግሯል።

የቫይረሱ ሥርጭት የተስፋፋበቸው ከተሞችን በመለየትና በካርታ በማስደገፍ የሚያቀርብ በመሆኑ ማኅበረሰቡ ከቦታ ወደ ቦታ ሲንቀሳስ ጥንቃቄ እንዲያደርግም የሚረዳው መሆኑን ገልጿል።

ውኃና ሣሙና በመቀላቀል ከንኪኪ ውጭ የሚሰራ 20 የእጅ መታጠቢያ በመሥራት ለአገልግሎት ማብቃቱን ያስረዳው ደግሞ ሻምበል መኮንን ተክለማርያም ነው።

ወጣት አሰፋ ተአምር በበኩሉ ኅብረተሰቡ በብዛት በሚንቀሳቀስባቸው ቦታዎችና ብዙ ሠራተኞች በሚገኙባቸው ተቋማት ውስጥ ፀረ ተሕዋስያን መርጫ መሣሪያ በመሥራት ለአገልግሎት ማብቃቱን ተናግሯል።

የፈጠራ ውጤት ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል የመሰቦ ሲሚንቶ የሽያጭ ሠራተኛ አቶ ኢሣያስ ሐጎስ በሰጡት አስተያየት ከንኪኪ ነፃ የሆነ የእጅ ማስታጠቢያ የፈጠራ ውጤት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።


የፈጠራ ውጤቱ በራሱ ጊዜ ሣሙናና ውኃ በመቀላቀል ከንኪኪ ውጭ እጅ የሚያስተጥብ በመሆኑ ተገልጋዮች ከሥጋት ነፃ በሆነ መንገድ እየተጠቀሙበት እንደሚገኙ አስረድተዋል።


በወጣቶች ፈጠራ የተሰራው የእጅ ማስታጠቢያ የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል  አስተዋጽኦ እንደለው በማመን እየተጠቀሙበት መሆኑን የገለጹት የሬድ ስታር ንግድ ድርጅት ሠራተኛ ወይዘሮ ሁሩት በላይ ናቸው።